በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለሀገር እና ለወገን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በየዓመቱ እውቅና እና ሽልማት እየሰጠ የሚገኝው ጷጉሜን የኢትዮጵያውያን መዝናኛና ባሕል ማዕከል (Pagumen Ethiopian Entertainment and Cultural Center (PEEC) የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም (ፌብሩዌሪ 21 ቀን 2006 ዓ.ም) በካሊፎርንያ ግዛት ሎሳንጀለስ ከተማ በተዘጋጀው የ7ኛው ዙር የእውቅና ሥነ-ሥርዓት እና የጷጉሜን ሽልማት (Pagumen Awards) 10ኛ አመት ምሥረታ ክብረ-በዓል የሽልማት ፕሮግራም ለሰባት ኢትዮጵያውያን እውቅናና ሽልማት አበርክቷል::
ሽልማቱ የተሰጣቸው ሰባቱ ኢትዮጵያውያን :-
- አቤል ብርሃኑ (የወይኗ ልጅ) ፦ በቱሪዝም ዘርፍ ተጓዡና የዩቲዩብ ይዘት ፈጣሪው አቤል ብርሃኑ፤ ከ86 በላይ የዓለም ሀገራትን በመዘዋወር፣ ታሪካዊ ሥፍራዎችን ለኢትዮጵያውያን በማስተዋወቅ እና መረጃን ተደራሽ በማድረግ ለቱሪዝም ዘርፉ ላበረከተው አስተዋጽኦ የዘንድሮው ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።
- ጌታቸው ወልዩ ፦ በጋዜጠኝነት ዘርፍ አንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ጌታቸው ወልዩ፤ ለ40 ዓመታት በጋዜጠኝነት፣ በታሪክ፣ በወታደራዊ ጉዳዮችና በዓባይ ተፋሰስ ጥናትና ምርምር ዘርፎች ሀገሩን በታማኝነት፣ በቅንነትና በትጋት ያገለገለ ሲሆን፤ ባበረከተው ዘመን ተሻጋሪ አገልግሎት የዘንድሮው “የጳጉሜን አዋርድ” የጋዜጠኝነት ዘርፍ ተሸላሚ ሆኖ ተመርጧል።
- አርቲስት ተፈሪ አስፋ (በድኅረ-ሕይወት /Posthumous) – ባለፈው ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አንጋፋው የሙዚቃ ሊቅ እና ተመራማሪ አርቲስት ተፈሪ አስፋ፤ በኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት ላይ ላበረከተው የማይተካ ሚና በሙዚቃ ዘርፍ በስሙ የክብር ሽልማት ተበርክቶለታል።
- ዶክተር ሐዋኒ ንጉሤ – “Early Childhood Education in Ethiopia”
የተሰኘ ግብረ-ሠናይ ድርጅት በማቋቋም፣ ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት እና ሕጻናትን በማስተማር ለትውልድ ግንባታ ላደረጉት አስተዋጽኦ የዘንድሮው የጷጉሜን ሽልማት “በበጎ አድራጎት እና ትምህርት ዘርፍ” ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። - አቶ ወልደገብርኤል አስጌ:- ደራሲ ወልደገብርኤል አስጌ፤ ከ62 ዓመታት በፊት “የነብዩ መሐመድ ታሪክ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ አማካኝነት ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪካዊ ሰነድ በማኖር ላበረከቱት አስተዋጽኦ፤ በሥነ-ጽሑፍ እና ታሪክ ዘርፍ የዘንድሮው የጶጉሜን ሽልማት የክብር ተሸላሚ ሆነዋል።
- ጋዜጠኛ ተወልደ በየነ (ተቦርነ)፦ ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያን ሙዚቃ ታሪክ በጥልቀት በማጥናት፣ በመመርመርና ታሪካዊ የድምጽና የምስል ቪዲዮዎችን ሰንዶ በማቆየት፤ በተለያዩ ሚዲያዎች ለሕዝብ እንዲደርስ በማድረግ ላይ የሚገኘው፤
የሁሌ አዲሱና የምንጊዜም ሚዲያው ተወልደ በየነ ላከናወነው ሀገራዊ አስተዋጽኦ “በሰነድና ማኅደር ማቆየት ዘርፍ” የዘንድሮው የጳጉሜን ሽልማትን አግኝቷል።- አቶ ፍስሐ ወልደ-አማኑኤል – የኢትዮዽያ የእግር ኳስ ታሪክ ሲነሳ ስማቸው ገዝፎ ከሚነሱ አንጋፋ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ፍስሐ ወልደ አማኑኤል በስፖርቱ ዘርፍ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የዘንድሮ የጳጉሜ አዋርድ የስፖርት ዘርፍ ተሽላሚ ሆኗል።
ተሸላሚዎች እንኳን ደስአላችሁ።
