ግዮን መጽሔት :- አዲሱን የኢትዮጵያ ዓመት ስንቀበል፣ ለውዷ ኢትዮጵያችንና ለሕዝቦቿ ለሰጠን ሕይወት፣ በረከት፣ ብልጽግናና ጥበብ ሁሉ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና እናቅርብ።
አዲስ ዓመት ለእኛ የዓመት መለወጥ ብቻ አይደለም። የጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ታሪክ፣ መንፈሳዊ ቅርስና ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈውን እምነታችንን የምናስታውስበት የተቀደሰ ጊዜ ነው።
ይህ ታሪክም የሳባ ንግሥት የሆነችው ንግሥት ማክዳ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ቤት ካደረገችው ታሪካዊ ጉዞ እና ከዘመናት በላይ ከቆየው የእምነትና የትውፊት ቅርሳችን ጋር በጥልቅ የተያያዘ ነው።
የአዲሱን ዓመት በረከት ስናከብር፣ እርስ በርሳችን ያለብንን ኃላፊነትም እንዘክር።
ጦርነት ባለበት ሰላምን እንፈልግ፤ መከፋፈል ባለበት መግባባትን እንፈልግ፤ ሥቃይና መከራ ባለበት ርኅራኄን እናሳይ። የትም ቦታ ብንሆን፣ ባልንጀራችንን እንደራሳችን እንውደድ።
ይህ አዲስ ዓመት ለኢትዮጵያ ሰላምን፣ ለሕዝቦቿ ብልጽግናን፣ ለልጆቻችን ደህንነትና ጥበቃን፣ ለቤተሰቦቻችን ጥንካሬን፣ ኢትዮጵያን ቤታቸው ላደረጉ ሁሉ ደግሞ በረከትን ያምጣ።
ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያን በሰላም፣ በፍቅር፣ በብልጽግና ወደተሞላ አዲስ ዓመት ይምራት። ለሀገራችን ሰላምን፣ ለሕዝቦቿም አንድነትና ተስፋን ይስጥ።
መልካም አዲስ ዓመት!
አዲሱ ዓመት በበረከት፣ በሰላምና በፍቅር የተሞላ ይሁን!!
ሸኔል ወለተ ሐና/አፍሪካ አሜሪካዊት
በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ። አሜን!!
አዲሱን ዓመት ስንቀበል፣ የአፋችን ቃልና የልባችን ሐሳብ በፊትህ ተቀባይነት እንዲኖረው እንለምናለን። አቤቱ፣ በሰላም፣ በደስታ፣ በሙላትና በበረከት አዲሱን ዓመት እንድንጀምር አድርገን። ካለፈው እንድንማር፣ በረከቶቻችንን እንድናስብና ከጭንቀታችን ይልቅ ተስፋችንን እንድናይ እርዳን።
አባታችን ሆይ፣ መስቀሎቻችንንና ሸክሞቻችንን ለመሸከም ብርታት ስጠን፤ ይቅር ማለትን፣ መማርንና ፍርድን ለአንተ መተውን አስተምረን። ወላጆቻችንን፣ ቤተሰቦቻችንን፣ መሪዎቻችንንና ሁሉንም ፍጥረታትህን በፍቅርና በአክብሮት እንድንይዝ እርዳን።
አቤቱ ሆይ፣ ምራን፣ ጠብቀንም። በእኛና በዓለም ላይ ሰላም፣ ብልጽግና፣ ፍቅርና አዲስ በረከት ይሁን። የጦርነት ሰለባዎች ነፃነትን ያግኙ፤ ጥበብና ማስተዋል ለሁሉም፣ ለጠላቶቻችንም እንኳን ይሰጥ። ልጆቻችን በደስታ ፈገግ ይበሉ፣ በሰላም ያድጉ፣ ንጽሕናቸውንም ይጠብቁ።
በዚህ ዘመን የምንኖረውን ሕይወት በጥበብ እንድንረዳ፣ የቃልህንም እውነት በጥልቀት እንድናውቅ አስተምረን። ኃይላችን፣ መጠጊያችንና ተስፋችን ሁን። እንደ ምሕረትህ አስበን፣ እንደ ኃጢአታችን አትፍረድብን።
በዚህ አዲስ ዓመት የበለጠ ፈገግ እንድንል፣ በደስታ እንድንስቅ፣ በጽናት እንድንጸልይ፣ ሩህሩህ፣ ደፋር፣ ትሁትና ሰላም ወዳድ እንድንሆን እርዳን። የጀመርናቸውን ሥራዎች እንድንፈጽም፣ መልካም ዕቅዶቻችንንም እንድናሳካ አግዘን።
ለወንድሞቼና ለእኅቶቼ፣ ለጓደኞቼ፣ ለቤተሰቦቼ፣ ለምወዳቸውና ለሚወዱኝ ሁሉ፣ እንዲሁም የተረሱ ለሚሰማቸው ሁሉ መልካም፣ ሰላማዊ፣ የበለጸገና በእውነት የተባረከ አዲስ ዓመት እመኛለሁ።
ወደ አዲሱ ዓመት በበለጠ ፍቅር፣ ጥበብ፣ መረዳትና ኃላፊነት እንራመድ። ሁላችንም በፍጥረት አንድነት የተሳሰርን መሆናችንን እንዘክር፤ በፍቅርና በእምነትም እንቀጥል።
አንድ ፍቅር፤
አንድ ሕይወት፤
ገብረሥላሴ (ካረቢያን)
መልካም አዲስ ዓመት!!
2019 ዓ.ም. በበረከትና በሰላም የተሞላ ይሁን፤
በዚህ አዲስ ዓመት በተሻለ መንገድ በጋራ መሥራትን እንድንማር፣ ለመፈወስና ያለፈውን ህመም በሰላም ለማስተናገድ የሚያስችሉ ደህንነትና መተማመን የሰፈነባቸውን ምቹ ሁኔታዎች እንድንፈጥር እመኛለሁ።
ለሕዝቦቻችን ዘላቂና ፍትሐዊ ልማት የሚያግዙ አዳዲስና ሰላማዊ መንገዶችን እንድንፈልግ፣ በዓለማችን የሚካሄዱት ብዙ ጦርነቶች እንዲቆሙ፣ ለሴቶቻችን፣ ለልጆቻችንና ለወንዶቻችን ፍቅር፣ ሰላምና ደህንነት የሰፈነባቸውን ማኅበረሰቦች እንድንገነባ እመኛለሁ።
ኒኪታ/ወለተኪዳን፤
(ባህማስ ደሴት)
ለኢትዮጵያውያን ውድ ወገኖቼ ሁሉ መልካም በዓል!!
ይህን ልዩ የ13 ኛው ወር ጳጉሜን ቀናት ስንጨርስ፣ ሁላችንም መንፈሳችንን አንጽተንና አድሰን ወደ 2019 ዓ.ም. እንድንገባ እጸልያለሁ።
ይህ አዲስ ዓመት አፍቃሪና መሐሪ እግዚአብሔራችንን በትጋትና በታማኝነት በማገልገል የምናሳይበት ዓመት ይሁን። ልባችን በምስጋና የተሞላ፣ በትሕትና የተሸለመ እና ሁልጊዜም ለመማር ዝግጁ ይሁን።
እግዚአብሔር አባታችን ሆይ፣ ላደረግህልን ሁሉ እናመሰግንሃለን። አሜን!!
በመላው ዓለም ላላችሁ ወገኖቼ መልካም አዲስ ዓመት እንዲህንላችሁ ምኞቴ ነው!!
ሥርጉተሥላሴ/አሜሪካዊት
መልካም አዲስ ዓመት!!
አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ፣ ባህልና መንፈሳዊ ቅርስ እንድናስብ፣ ያለፈውን እንድንማርበትና በተስፋ ወደፊት እንድንጓዝ ያስታውሰናል፤ ያበረታናል።
ከአፍሪካዊው የአንድነት፣ የUbuntu እሴት— “እኔ የሆንኩት እኛ ስላለን ነው!”— ፍልስፍና ተምረን ፍቅርን፣ መተሳሰብንና ሰላምን እናጠናክር።
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት እንደ አዲስ ገጽ ለእያንዳንዳችን ብርሃን፣ ጥበብ፣ ጤና፣ ብልጽግናና ሰላም ይዞ ይምጣ። በእምነታችን ጸንተን፣ በባህላችን ኮርተን፣ በአንድነታችን በርትተን ለተሻለች ኢትዮጵያና ለሰላማዊት አፍሪካ እንስራ።
እንኳን ለ2019 ዓ.ም. አዲስ ዓመት አደረሳችሁ!! ዓመቱ ለሁላችንም የበረከትና የሰላም ይሆንልን ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው!!
ዶ/ር ደስታ ማጉሆ (የቦብ ማርሌይ ቤተሰብ)
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 236 መስከረም 2019 ዓ.ም
