ግዮን መጽሔት :- አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ብቻ ሳይሆን የኅሊና መመርመሪያ፣ ያለፈውን መለስ ብሎ ማያ እንዲሁም መጭውን ጊዜ በተስፋና በብርሃናዊ ርእይ ለመቃኘት የሚጣደፉበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡ የ2018 ዓ.ም የዘመን ገጽ ተዘግቶ አዲሱ 2019 ዓ.ም ሲከፈት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ያህል ውስብስብ ከሆኑ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች፣ ድንቅ የቴክኖሎጂ ዕድሎች እና ማኅበራዊ ውጥረቶች ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጣ ትገኛለች፡፡ ይህንን የታሪክ መጋጠሚያ መሠረት በማድረግ «ግዮን» መጽሔት በልዩ ልዩ ዘርፎችና ሙያዎች ውስጥ ከሚገኙ አራት የሀገራችንን ታዋቂና አንጋፋ ባለሙያዎች ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጋለች፡፡ መልካም ንባብ!
ለዛሬ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉን አቶ ክቡር ገና ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል ። መልካም ንባብ !
ግዮን፦ በ2018 ዓ.ም በጣም ያዘኑበትን እና የተደሰቱበትን አጋጣሚ ቢያካፍሉን?
ክቡር፡- ደስ ያለኝ ለማለት የሚያስቸግር ቢሆንም፣ በ2018 ዓ.ም እንደ በጎ ነገር ያየሁት ከኤርትራ ጋር ሊደረግ የነበረው ጦርነት ሳይካሄድ መቅረቱ ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ ሁኔታ ይቀጥላል የሚል እምነትም አለኝ፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ዓመት በእጅጉ የሚያሳዝነኝ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅም ሆነ በሁሉም አቅጣጫዎች እየተካሄደ ያለው ጦርነትና ይዞት እየመጣ ያለው መጥፎ ተጽዕኖ (ጦስ) ነው፡፡
ግዮን፦ በዚህ «ዲጂታል» ዘመን ከንባብ የራቀ ትውልድ መበራከቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያስከትለው ችግር ምንድን ነው ይላሉ?
ክቡር፡- በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የንባብ ባህል እየደከመ መምጣቱ ይታያል፡፡ በመሠረቱ የኮምፒውተር ተጠቃሚ የሆነው ማኅበረሰብ በዚሁ ቴክኖሎጂ ነው የሚመራው፤ ዜናውም ሆነ መዝናኛው የሚቀርብለት በዚሁ መንገድ ነው፡፡ ብዙዎች ይህንን እንደ ችግር ላያዩት ይችላሉ፤ ነገር ግን ምንጩና ጸሐፊው በማይታወቅ መረጃ ላይ ተመስርቶ መመራት አደገኛ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ትልቁ ችግር ግን በንባብ የሚገኝ እውቀት ከቀረ የሀገር እድገት ወደ ኋላ መጎተቱ ነው፡፡ ማንበብ የማይወድ ትውልድ ምርመርና ጥናት ማድረግ አይችልም፡፡ ጥናት ማድረግ የማይችል ወጣት ደግሞ ከዓለም ጋር ያለው ተወዳዳሪነት እጅግ የወደቀ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የማያነብ ትውልድ ሀገርን ለችግር ይዳርጋል፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥትም ሆነ ወላጆች አዲሱ ትውልድ በንባብ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የማነቃቃት፣ የማሰልጠንና የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ግዮን፦ ማኅበራዊ ሚዲያ ከመደበኛው ሚዲያ ይልቅ አጀንዳ አፍላቂ መሆኑ ምን ያህል ቀውስ አስከትሏል ብለው ያስባሉ?
ክቡር፡- ትክክል ነው፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ዋነኛ አጀንዳ ፈጣሪ ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ የበለጠ የሚያሳዝነው የቀረበው አጀንዳ ገዥ ማግኘቱ ነው፡፡ ትውልዱ ፈረንጆች “consumer” እንደሚሉት ዜና አፍላቂ ሳይሆን የቀረበለትን መረጃ ብቻ የሚቀበል ተመልካች ሆኗል፡፡ አንድን ሀገር ማስተሳሰር የሚችሉት እንደ እድርና እቁብ ያሉ ሀገር በቀል ማኅበራዊ ስብስቦች ናቸው፡፡ በዲጂታሉ ዓለም ግን ሀገርን ማሰባሰብ ሳይሆን የመበታተን አዝማሚያ ነው የሚታየው፡፡ ይህንን ቀውስ ለመታገል እያንዳንዱ ግለሰብ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕብረተሰቡ ማኅበራዊ ሚዲያን ሲጠቀም የእውቀት አድማሱን የሚያሰፉ አዎንታዊና ትምህርታዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ግዮን፦ ሀገሪቱ ከአሁኑ ምስቅልቅል አልፋ የተረጋጋ ነገን ለመገንባት «ሊተዉት» እና «ሊይዙት» የሚገባቸው እሴቶች ምንድን ናቸው?
ክቡር፡- በብሔርና ብሔረሰብ ማንነት ላይ ያተኮረው የዘር ሽፋን እንቅስቃሴ እንዴት መታረም አለበት የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ በእርግጥ በብሔረሰብ ላይ የተመሠረተ አስተዳደር የደነገግነው እኛ ብቻ አይደለንም፤ በዚህ መልኩ የተዋቀሩ በርካታ ሀገራት አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ሀገራት ትኩረት የሚያደርጉት የሚያሰባስባቸውና አንድ የሚያደርጋቸው እሴት ላይ ነው፡፡ በእኛ ሀገር ግን ሀገራዊ ዜግነት ከብሔር ማንነት በታች ሆኗል፡፡ ሥልጣን፣ ግዛትና አጠቃላይ ፖለቲካው በብሔር መነጽር ማየት ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የብሔር አጥር ሀገራዊ ዜግነትን ጋርዶታል፡፡ ሕገ-መንግሥቱም በዚህ መንገድ የተቀረጸ በመሆኑ፣ መንግሥትም በሚጠበቀው ልክ እየሠራበት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ቀጣዩን ትውልድ ወደ አደገኛ ግጭት ይከተዋል ብዬ እሰጋለሁ፡፡
ግዮን፦ ከሀገራችን የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ጋር ተያይዞ በእጅጉ የሚያሳስብዎት ምንድን ነው?
ክቡር፡- በሀገራችን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚያሰባስቡ ሀሳቦችና ስብስቦች ነበሩ፤ አሁን ግን እነዚህን አሰባሳቢ እሴቶች እያጣናቸው ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ስብስቦች እንደገና ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ የሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎችን ስንመለከት፣ ማኅበረሰቡ ከአካባቢው እንዲነሳ ሲደረግ ቤተክርስቲያኑንና ማኅበራዊ እሴቶቹን ትቶ ይሄዳል፡፡ ይህም የነበረውን ማኅበራዊ ስብስብ እንደማፍረስ ይቆጠራል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አቀራረብ በከተማ መሪዎቻችን ዘንድ እንደ ችግር አልታየም፡፡ ነገር ግን የእድገት መሠረቱ ሕንፃዎችን ማስዋብና ማብለጨለጭ ብቻ አይደለም፡፡ ለእድገት ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የከተማው ነዋሪ የተሰጠውን ዕድሜ በአግባቡ ተጠቅሞ ሕይወቱን የሚያሻሽልበት እድል ላይ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት የተገነባውን ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴት ማፍረስ ትክክል አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡
ግዮን፦ በዚህ በተዳከመ የሕትመት ሚዲያ ዘርፍ እንደ ግዮን ያለ መጽሔት ሕልውናውን አስጠብቆ እንዲቀጥል ምን መደረግ አለበት?
ክቡር፡- መጽሔት መቼም ቢሆን ፈጣን ዜና አቅራቢ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም የሚታተመው በሳምንት ወይም በወር አንዴ ነው፡፡ ፈጣን ዜናዎች ደግሞ በዲጂታል ሚዲያው ይሸፈናሉ፡፡ ስለዚህ በመጽሔት የሚቀርበው ይዘት ምን መሆን አለበት የሚለው መጠናት አለበት፡፡ በእኔ እምነት መጽሔቶች ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ከአንድ ክስተት ጀርባ ያሉትን «እንዴት?» እና «ለምን?» የሚሉ ጥልቅ ጥያቄዎች ላይ ነው፡፡ አንድ ነገር ሲከሰት «እንዴት ተከሰተ?»፣ «ምንስ ውጤት ያመጣል?» የሚሉ ትንተናዎችንና ጥልቀት ያላቸውን ሀሳቦች ማቅረብ መቻል አለባቸው፡፡
ግዮን፦ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ምን መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ?
ክቡር፡- የአዲስ ዓመት (የእንቁጣጣሽ) በዓል ዋነኛ ዓላማ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማሰባሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን በዓል ሁላችንም በደስታ፣ እንዲሁም ያጡና የተቸገሩ ወገኖቻችንን በማሰብና በመደገፍ ብናሳልፈውና ይህንን የቆየ የደግነት ባሕላችንን ብናሳድገው ደስ ይለኛል።
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 236 መስከረም 2019 ዓ.ም
