መንግስት የንግዱን ማህበረሰብ ችግር ደረጃ በደረጃ እየፈታ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር “የንግዱ ማህበረሰብ ሚና፤ ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የማጠቃለያ መድረክ እያካሄደ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ማህበረሰብ አካላት ከወረዳ ጀምሮ በየደረጃው ከመንግሥት ጋር ወይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
በዛሬው ዕለት የማጠቃለያ መድረኩ ሲካሄድ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ የንግዱ ማህበረሰብ በየደረጃው በነበረው ውይይት ላይ ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ እየሰጠ ይገኛል።
መንግሥት የንግዱን ማህበረሰብ ችግር ከመፍታት ጎን ለጎን ምቹ የስራ ቦታን እየፈጠረ ይገኛል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ የንግዱን ማህበረሰብ ችግር ደረጃ በደረጃ እየፈታ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የነበሩ የመብራት መሠረተ ልማት፣ የሰሠራር መጓተት፣ ግብርን በተመለከተ ያሉ ችግሮችን መንግስት እያሻሻለ ይገኛል ብለዋል።
የግብር አሰባሰብን በማሻሻል ምቹ የንግድ ስርአት እየተዘረጋ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በብልሹ አሠራር ተሳትፈው የተገኙ ከ160 በላይ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።
ባለፍት ሰባት ዓመታት የግብር አሰባሰብን ከ30 ወደ 260 ቢሊዮን ማሳደግ ተችሏል፤ በዚህም የከተማው መሰረት ልማት ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
እንደ ሀገር ውጤታማ ሥራ ለመስራት መንግስት እና የንግዱ ማህበረሰብ ተቀራርበው መስራት እንደሚኖርባቸው ገልፀዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የንግድ ማህበረሰብ አባላት እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውን በመግለፅ፤ የምንከፍለው ግብር በትክክል ለልማት እየዋለ መሆኑን ተረድተናል ሲሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም ምቹ የሥራ ከባቢ መፈጠሩንና በሁሉም ዘርፍ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ነጋዴዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የንግድ መስሪያ ቦታ ችግር እንዲቀረፍ፣ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ የአገልግሎት መጓተቶች እንዲሻሻሉ፣ ህጉን ጠብቀው የማይሰሩ ነጋዴዎች ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡና ነጋዴው ይበልጥ እንዲደገፍ ጠይቀዋል።
