ሙዚቃ እና ዘመን ሠሎሞን ለማ ገመቹ

Date:

 

ግዮን መጽሔት :-     ይህ ርዕስ ወደ ጥልቅና ሰፊ የሙዚቃና የዘመን ቁርኝት ዕይታና ትንታኔ ሊመራ የሚችል መሆኑ ርግጥ ነው፡፡ የሙዚቃ እና የዘመንን ሕብር እንዲህ እንደ ዋዛ ብድግ ጣል ማድረግ አይቻልምና ርዕሱን እንደ ምጥንና ቁጥብነቱ ገርመም አርጎ ማለፉም ይሁን እጅግ በርቀትና በጥልቀት ሊተነተን የሚችል ጉዳይ ሊሆን ይችላል ብሎ ከአንድ ወሳኝ መደምደሚያ ላይ መድረሱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡

የሆነ ሆኖ… ሙዚቃን አዲስ ከምንለው ዓመት መባት ወይም መምጣት ጋር በተጎዳኘ ያለውን እና የነበረውን ብሎም ለወደፊትም የሚኖረውን ዋጋ በዘመን ልኬትና ስሌት በድርበቡ መመልከቱ ጥሩ ነገር ሆኖ ይሰማኛል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ፤ የዘመናዊነትን ጉዞ ከጀመረች ውሱን ዓመታትን ማለትም፡- ግፋ ቢል ሰማኒያ ስድስት፤ አነሰ ቢባል ደግሞ ሰማንያ አንድ ያህል ዓመታትን ያስቆጠረችውን የኢትዮጵያችንን ሙዚቃ ዘመናዊ መልክና ቅርፅ በውሱን ደረጃ ዳሰስ ማድረጉ ከያዝነው 2019 ዓ.ም አጠቃላይ ድባብ አንፃር ተገቢ ነው የሚል ግምትም ወስጃለሁ፡፡

ከርዕሰ-ጉዳዩም ጋር በተቀራረበ አብዛኛውን ጊዜ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዚዮን ብሎም አሁን አሁን በማኅበራዊ ሚዲያ ጎላ ብሎ የሚሰማውን የጥላሁን ገሠሠን ዜማ እንደመንደርደሪያ ይሆን ዘንድ ከዚህ በታች አስፍሬአለሁ፡-

‹‹ክረምት አልቆ በጋ – መሥከረም ሲጠባ

አሮጌ ዓመት አልፎ – አዲሱ ሲገባ

በአበቦች መዓዛ – ረክቷል ልባችሁ

‹ሰዎች› ሁሉ በጣም – ዕንኳን ደስ ያለችሁ!››

 

‹‹የበሽታን ዓይነት – በሙሉ ጠራርጎ

ከቁሻሻ ጋራ – ጎርፉ ሙልጭ አርጎ

ፈሳሽ የወንዝ ውሃ – ተውሳኩን ይውሰደው

ጤና መሆንን ነው – እኛ የምንወደው

‹‹—-

—-››

‹‹ዘለዓለም አይጉዳን – ገብቶ በሽውታ

ተነቅሎ ይጥፋልን – የሳንባ በሽታ

ጉንፋን ኢንፉሌንዛ – ቁርጥማቱ ሁሉ

የጨጓራም ሆነ – የጉበት በሙሉ

‹‹—-

—-››

‹‹የበሽታ ዓይነት – ካልወደመልን

አይችልም ጤናችን – ሊመለስልን

የደም ብዛትና – እንዲሁም ማነስ

ከሃገራችን ይጥፋ – ሕዝብን ሳይጨርስ

‹‹—-

—-››

ይህ የዘመንን ሽግግር፣ የዓመታትን መሸኘት መምጣት …፤ ከሰው ልጆች መንፈሳዊ ዕርካታ፣ ተፈጥሮ ያለ ልዩነት ለሁሉም ከምትሰጠው ውበት፣ ከምታመነጨው መዓዛ፣ ከምታድለው የጤና በረከት፣ ከክረምት በጋው ወቅት መፈራረቅ አኳያ ስለሚኖረው አስደሳች ስሜትና ተስፋ … በጥዑም ዜማ ፍሰት ታጅቦ ሰዋዊ መልዕክቱን የሚያንቆረቁረው የጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ፤ በዘመንና በራሱ በሙዚቃ መካከል የነበረን፣ ያለና የሚኖርን መስተጋብር በጉልህና በደማቅ የሚያሳይ ነው፡፡…

የአያሌ የሙዚቃ ዜማና ግጥም ደራሲያን፣ የሙዚቃ ቀማሪዎች፣ አዛሚዎችና አንጎራጓሪዎች ድንቅ ሥራና ተግባር በዘመን ውስጥ ያለው የላቀ ሥፍራ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ በሻምበል አፈ-ወርቅ ዮሐንስ ግጥሞቻቸው ተከትበው፣ በሌሎች የሙዚቃ ሙያተኞች ውብና ማራኪ ዜማ ተሠርቶላቸው፣ በመልዕክታቸው ወይም በሐሣባቸው ውበትና ጥንካሬ… መጠን በአግባቡ የተቀመሩና የተስተካከሉ ድንቅ ሙዚቃዎች፤ ያለፈውን ዘመን የምንቃኝባቸው፣ በዘመኑ የኖረውን ወገን ግላዊ፣ ማሕበረሰባዊ ምልከታ አጠንቅረን የምንመለከትባቸውም ሆነ የምንመዝንባቸው ናቸው፡፡

የፍቅርን፣ የናፍቆትን፣ የኑሮን ተለዋዋጭ ስሜታዊ መልኮች ከሚያሳዩና ከሚነግሩ… ሙዚቃዎች መካከልም በሻምበል አፈ-ወርቅ ግጥሞቻቸው ተጽፈው… ዘላቂነት ባለው ሕያው ስሜታዊ ትርጉማቸው ኃይል ከዚያኛው ዘመን ወደዚህኛው ዘመን የደረሱ አሉ፡፡ መድረስ ብቻ ሳይሆን በተወዳጅነታቸው እና በልዩ ተመራጭነታቸው ልቀው መገኘትም ችለዋል፡፡

በዚህ ሚዛን ልክ ተመዝነው፣ በዘመን ውስጥ በይበልጥ እንደ ተወዳጅ የወይን ጠጅ ባለ ግሩም ጣዕምና ለዛ ሆነው፣ በዚህኛው ዘመንም እንደተፈጠሩበት ዘመን ጎልተው እና ደምቀው፣ በብዙኃኑ አድማጭ ተወዳጅና ተመራጭ ሆነው ዘወትር እንደ አዲስ ከሚቀነቀኑት ሙዚቃዎች መካከል ለአብነት ያህል ከሚጠቀሱት የሻምበል አፈ-ወርቅ ሥራዎች መካከል፡- ‹‹ነሽ አምሳሉ፣ የልቤን አዳራሽ መኖሪያ አርጋዋለች፣ እዩዋት ስትናፍቀኝ፣ ዕንኳን ቆሜ ብሞት ብቀበርም፣ ፍቅሬ ለመሆንሽ እርቀሽ ሳትሄጂ፣ ምንም ሀብት ቢሞላኝ ምንም ቢደላኝ፣ ኡኡታ አያስከፋም፣ አንቺ እኔን ውደጂ እኔም ልውደድ አንቺን፣ መለያየት ሞት ነው፣ የትዝታዬ እናት፣ ፍቅር የጋራ ነው አይደለም የብቻ፣ የዘገየሽበት ምን ይሆን ምክንያቱ፣ የጠላሽ ይጠላ ፣ ሰላምታዬ ይድረስ ናፍቆቴን ያስረዳ ፣ ካንድም ሁለት ሦስቴ ፍቅር ደርሶብኛል ፣ የሕይወቴን ተስፋ ፍቅሬን አጣኋት፣ የትዝታዬ እናት›› ሌሎችም የሚጠቀሱ ይሆናሉ፡፡

የአዲስ ዘመንን መባት… አመላካችና ገላጭ ሆነው ከሚታዩት የዘሪቱ ጌታሁን ‹‹ዕንቁጣጣሽ ዕንኳን መጣሽ›› እና የሐመልማል አባተ ‹‹የክረምቱ ወር አልፎ የበጋው መጥቷል…›› ዓይነት ተወዳጅና ምሉዕነት ያላቸው የኪነ-ጥበብ በረከቶችም ይሁን እንደሌሎቹ መሰል ሥራዎች ሁሉ፤ ሙዚቃ የነፍስ ወይም የስሜት ዜማዊ ውህደት ውጤት ነው፡፡ ነፍስና ስሜት ደግሞ የሕያውነት አካል እንደመሆኑ፤ ሙዚቃ በራሱ ሕይወት ነው፡፡ በሌላ የመግለጫ ቃል ሙዚቃ የነፍስ ዝማሬ፣ ሙዚቃ የስሜት ወካይና ገላጭ ቋንቋም ነው፡፡ ሙዚቃ ምኞትን ወካይ፣ ሕልምን ገላጭና ፈቺ፣ ተስፋን አመላካችና ተንታኝም ነው፡፡

ያም ብቻ አይደለም፡፡ ሙዚቃ… የሰው ልጆችን የወል የሆነ ሐሣብና አመለካከት፣ ደስታና ተድላ፣ ኃዘንና ትካዜ፣ ጭንቀትና ሕመም፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ ብቸኝነትና አብሮነት፣ መድከምና መበርታት፣ መጠቃትና ድል-አድራጊነት፣ ማግኘትና ማጣት፣ መራብና መጠማት፣ መከራና መገፋት፣ ጥረት-ትግልና ውጤት፣ መታመንና መከዳት፣ ዕንባና ፈገግታ፣ ትዳርና ቤተሰብ፣ መንጣትና መጥቆር፣ ማበብና መጠውለግ፣ ፍትሕና በደል፣ መታሰርና መፈታት፣ መድልዖና ዳኝነት፣ ነፃነትና ባርነት፣ ምቾትና ጉስቁልና፣ መታወስና መረሳት፣ መናቅና መከበር… የሚገለጹበት ውብና ረቂቅ ሙያዊ ልሳን ነው፡፡

በተጨማሪም ሙዚቃ ሐሣቦች ማለትም የመኖር ግራ ቀኝ፣ ከፍታና ዝቅታ ወካይ አመለካከቶች የሚነገሩበት፤ ማራኪ፣ ሳቢና ስሜትን ኮርኳሪ ዜማዊ ልሳን ስለሆነም  ‹‹የዓለም ሕዝብ ቋንቋ ነው›› የሚለውን አደላዳይና አሻሚ ያልሆነ ምስክርነት አግኝቷል፡፡ በዚህም ይሁን በሌላ መመዘኛ ወይም የሕይወት ዘርፈ-ብዙ ስሜታዊ መለኪያዎች መሥፈርት፤ ከሰው ልጆች የመወለድ፣ የመኖርና የመሞት ተፈጥሮአዊ ዑደት ጋር ዘመን ሊገድበው የማይችል ልዩና መስዕባዊ የሆነ … የመንፈስ ትስስር ያለው መሆኑም ተረጋግጧል፡፡

ሙዚቃ እንደ ‹‹የዓለም ቋንቋነቱ›› ሁሉ፤ የዚያኛውና የዚህኛው ዘመን፣ ያለፈውና የሚመጣው ዘመን ማስተሳሰሪያ ወይም ማቆራኛ አስደማሚ፣ ኃይለኛና ጠንካራ የስሜት ክርም ነው፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው?… ሙዚቃና ዘመን የማይለያዩ ናቸው እንደማለት ነው፡፡ ሙዚቃ አላፊው ትውልድ ከመጪው፣ ነዋሪው ከሟቹ… ያለ ዘመን ልዩነት ወይም ያለ ዘመን ገደብ፤ በሙዚቃ አማካይነት የሐሣብ ውህደታቸው፣ የስሜት አንድነታቸው፣ የፍላጎትና የባሕሪ ዝምድናቸው ሲወራረስ፣ ሲሳሳብ፣ ሲናበብ… ይታያል እንደማለትም ነው፡፡

እንዲህ ብሎ ማለት ግን… ባለፈውና በመጪው የሰው ዘር መካከል፤ ራሱን ሙዚቃን ታሳቢ በሚያደርገው ዐበይት ጉዳዮች ዙሪያ፤ ዘመናቱ እንደሚፈጥሩት ዕንግዳ ነገሮች… ፈቃድና አስገዳጅነት ከቶውንም ልዩነትና አዳዲስ የሙዚቃ ሥራ ክህሎቶች፣ የሙዚቃ አቀማመር ሥነ-ዘዴዎች፣ የሙዚቃ አጨዋወት ስልቶች የሉም ማለት አለመሆኑን፤ እንደ ጸሐፊው ሁሉ የዚህ ጽሑፍ አንባቢ የሆነው ወገን ሁሉ በተጨባጭ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባል፡፡

ከፍ ሲል የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሙዚቃ… ያለፈውን የሰው ልጅ፤ ባለፈበት ወይም በኖረበት ዘመን የወልም ይሁን የተናጠል  አኗኗሩ መልክና ቅርጽ፣ በኖረበትም ልማድ፣ ወግ፣ ሕግና ሥርዓት ልክ፤ የሕልውናውም አሰንባች ሆኖ በቆየው ተስፋ፣ ሕልም፣ ምኞቱ… ርቀትና ጥልቀት መጠን፤ የነበረ ማንነቱን፣ የሕይወቱን እንዴትነት አመላካችና ገላጭ ነው፡፡

ስለሆነም ዘመን በሙዚቃ፣ ሙዚቃም በዘመን ውስጥ ያንኑ የመሰለ ተለዋዋጭም ይሁን ተዛማጅ፣ ውህድም ይሁን ተሳሳቢ ወይም ደግሞ ተመጋጋቢ የስሜት ጓዞቹን… መሠረታዊ ይዘታቸውን ወይም ጠቀሜታቸውን ሳያፋልስ፤ ስልተ-ምታቸውን፣ ጣዕምና ለዛቸውን በመለዋወጥም ይሁን በማጉላት ከዘመን ወደ ዘመን ይሸጋገራል፡፡ ሙዚቃ ዘመኑን ይነግራል፡፡ ሙዚቃ ወደ ዘመን ይሻገራል፡፡ ሙዚቃ በዘመን ውስጥ የየጊዜውን ሰው ሐሣብ፣ ምኞት፣ ጉጉት፣ ብርታት፣ ጥረት፣ ጥንካሬ፣ ዕውቀት፣ ዕምነት፣ ተስፋ… እየገለጸ ዑደቱን ይቀጥላል፡፡

ይህ ሁሉ ሲባል ግን… ሙዚቃ የዜማ፣ የግጥም፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች እና በነዚሁ ዐበይት የሙዚቃ መሠረቶች ዙሪያ የሚኖሩ ሙያተኞች ተግባር ውህድ ውጤት መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ በሙዚቃ በሴትና በወንድ መሀል የሚኖር ሐሣባዊና ገቢራዊ … የፍቅር ጭውውት የሚገለጽበት ሰውኛ የመግባቢያ ኃይልነቱም የሚስተባበል አይደለም፡፡ ከዚህም ባሻገር የሰው ልጅ ሁሉ የሕይወት ትዝብት፣ ተስፋ፣ ምኞት፣ ልፋት፣ ጥረት፣ ትግል፣ ትካዜ፣ ተብሰልስሎት፣ ሐዘን፣ ደስታው፣ ብርታቱና ጀግንነቱ… የሚገለጽበትም ረቂቅ ጥበብ ነው፡፡ (‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ›› በተስፋዬ ለማ የተፃፈው መጽሐፍ በገጽ 47 እና 48 እንደሚያስረዳው…)

በብዙ አቅጣጫ ሊታይና ሊተነተን… የሚችለው ሙዚቃና ዘመን፤ ከሚዳሰስና ከሚቃኝበት አያሌ መስመሮች መካከል ተነቅሶ አንደኛው መስመር ሲታይና ሲመዘን ደግሞ የሙዚቃ ስልቱና አካሄዱ… በዘመን ውስጥ እንደየዘመኑ ሁነትና በዘመኑ ሂደትም እንደኖረው ሰው ሐሣብና አመለካከት፣ የስሜት ከፍታና ዝቅታ… ተለዋዋጭ ነው፡፡ መሠረቱ ግን አንድና ብቸኛ ነው፡፡ እሱም የሰው ልጅ ወይም የሰው ልጆች ውስጣዊ ዕይታ፣ ውጫዊ ምልከታ፤ ምኞት፣ ህልምና ህልማቸውን፣  ተስፋውን ወይም ተስፋቸውን… እንደየዘመኑ መልክና ቅርፅ የሚወክልና የሚዋጅ መሆኑ ነው፡፡

ይህም ማለት ምን ማለት ነው? … በዘመነ ምኒልክ እንደዘመነ ምኒልክ፣ በዘመነ ተፈሪ እንደዘመነ ተፈሪ፣ በዘመነ ደርግ አንደ ዘመነ ደርግ፣ በዘመነ ወያኔ እንደ ዘመነ ወያኔ … ሙዚቃ ከዜማና ከግጥም ፍልቀቱና ፍሰቱ ጀምሮ በሙያተኞች ሙያዊ የዕውቀት ደረጃና ችሎታ … አየተቀመረና እየተኳለ፤ ከሰው ለሰው በሰው አማካይነት ለሙዚቃ አፍቃሪው ወገን ገበያ የሚቀርብ፤ ለመንፈሱ ረሃብና ጥም አስፈላጊ የሆነ እህል ውሃ ማለት ነው፡፡

ለማንኛውም ከሙዚቃና ከዘመን ሐሣብ… አኳያ እጅግ ከረዥሙ በአጭሩ… በ2019 ዓ.ም መባቻና ዋዜማ የቀረበውን ይህንን ጽሑፍ ለመቀንበብ ያህል፤ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ሊቃውንት፣ የሙዚቃ ሥራዎች ታሪክ ተመራማሪ፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች መብት ተሟጋችም ጭምር የነበረው ተስፋዬ ለማ፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዓይነተኛ ባለውለታ ስለሆነው ቅዱስ ያሬድ እና ስለ ኢትዮጵያዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በዘመን ውስጥ የሙዚቃና የኪነ-ጥበብ ባለውለታነት… ያሰፈረውን ቃል በማሳረጊያው መንደርደሪያ ላይ አኑሬው ልለፍ፡፡

ተስፋዬ ለማ ‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ›› በተሰኘው የግንቦት ወር 2005 ዓ.ም መጽሐፉ በገጽ 92 በሁለተኛውና በአራተኛው አንቀጽ ላይ፡- ‹‹ቅዱስ ያሬድ በኖረበት ዘመን፤ ዓለም እንደ አሁኑ በጥበብ ልትራቀቅ ቀርቶ ዓይኗን ዕንኳ (በአግባቡ) አልገለጠችም ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ነው ኢትዮጵያ እንደ ቅዱስ ያሬድ ያለ ታላቅ ሊቅ ፈጥራ ነበር፡፡ እጅጉን ድንቅ የሆነው የቅዱስ ያሬድ ዝማሬ በየዘመናቱ እያደገና አየተስፋፋ ባይሄድም በኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን አማካይነት እስከ ዛሬ ድረስ ተጠብቆ መኖሩ ራሱ፤ ቤተ-ክርስቲያኒቱን ያስመሰግናታል፡፡… ቅዱስ ያሬድ የአውሮፓ ሰው ቢሆን ኖሮ ስሙ በመላው ዓለም እጅግ በገነነ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን… ትኩረቷ ቤተ-ክርስቲያንን ማስፋፋት ላይ ብቻ መሆኑ…   የቤተ-ክርስቲያኒቱ አባት የሆነው የቅዱስ ያሬድ ረቂቅ ሥራዎች የሚጠኑበትና ምርምር የሚደረግበት ተቋም አልከፈተችም፡፡ የዜማ፣ የቅኔ፣ የአቋቋምና የትርጓሜ መጻሕፍት ሊቃውንትም በቂ ደመወዝና እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው ተተኪዎችን ማፍራት አልቻሉም›› የሚለውን ቃል አስፍሯል፡፡

ይሁንና ተስፋዬ ለማም ይሁን ሌሎች በሙዚቃ እና በዘመን ውስጥ ሙዚቃው በነበረው ሚና ላይ የየራሳቸውን ታሪካዊ ዕውነት ያስቀመጡ ሰዎች፤ ያሉት የመሰከሩት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የሃገር፣ የወገን፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ሆኖ መታየት ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ ያደረገውን ጉዞ በመቀጠል፤ አሁን ‹‹ደርሷል›› የተባለበት… ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ የደረሰበት ምዕራፍ ሙዚቃና የሙዚቃ ሰዎችን፣ ሙዚቃና የሙዚቃ አፍቃሪዎችን… በሚፈለገውና በሚፈልጉት ልክ ጠቀመም አልጠቀመ፤ የሙዚቃና የዘመን፣ የትውልድና የሙዚቃ ቁርኝት ግን እንደቀጠለ ነው፡፡

ሲጠቃለል፣ ሙዚቃና ዘመንን በመንተራስ በመጠነኛ ቃላት ሕብር ያሰፈርኩት ጽሑፍ  እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በዘመን ውስጥ አንዱን ማኅበረሰብ ከሌላው ማኅበረሰብ በስሜት፣ በፍላጎት፣ የወል በሚሆነው የመሳሳብ ዑደት አማካይነት… የጋራ የሕልውና መሠረት የሆነውን ምግብን ምክንያት በማድረግ፤ ዜጎች ወዲያም ሆኑ ወዲህ በሕብረትም ይሁን በአንድነት መሆን እንዳለባቸው የሚሰብከውን… ሙዚቃ ሐሣብ በአግባቡ መመልከትና በውል ማጤን ይቻል ዘንድ የሙዚቃውን ግጥም ይዘት ከዚህ በታች ማስፈሩን ምርጫዬ አድርጌዋለሁ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት! ያሰንብትልኝ !!

‹‹አትክልትና ፍሬ – የሥጋ ብልቶች

ሞልቷል በሃገራችን – የምግብ ዓይነቶች››

 

‹‹ቀይ አልጫ ዱለት – ምንቸት አብሽ ጥብሱ

ቅቅልና እንፍሌው – ቅንጬውን ቢቀምሱ

የአማራ ዶሮ ወጥ – የበጉም ይጥማል

በቅመም ሲሠራ – እጅ ያስቆረጥማል

‹‹—

—››

‹‹በረጅሙ ዋንጫ – ጥሩ የገብስ ጠላ

መጠጣት ያፋፋል – ከምግብ በኋላ

ዕንኮይ የመሰለ – ጥሩ የማር ጠጅ

በፊት ጮማ በልቶ – መኮምኮም ነው እንጅ

‹‹—-

—-››

‹‹የትግሬ አንባሻ – ለሆ ያስጎመጃል

ዱቃና ጽራይም – አካል ያደረጃል

የጉራጌ ክትፎ – ሲቀርብ በገበቴ

በቆጮ ጠቅልሎ – ና ግባ በሞቴ

‹‹—-

—-››

‹‹የ‹ኦሮሞ› ላም ወተት – የቀዘቀዘ ዕርጎ

የነጠረ ቅቤ – በአናቱ ተደርጎ

ወደ ሆድ ሲልኩት – እያራሰ ይወርዳል

ጤንነት ሰጪ ነው – ትኩሳት ያበርዳል

‹‹—-

—-››

‹‹የሱማሌ ምግብ – የግመል ወተት

የማሽላ ገንፎ – የአደሬው ዕልበት

የ‹ወላይታው› ምግብ – ባጨራ ጉርዶራ …

አሙቾና ቡንዶ – ጥህሎ እንደ እንጀራ፤


ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 236 መስከረም  2019 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የመልካም አዲስ ዓመት መግለጫ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ታደሰ ብሩ (ዶ/ር)

  ግዮን መጽሔት :-   ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ እንኳን ለ2019 ዓ.ም....

‹‹የኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት ሕዝቧ ነው›› ዶ/ር ንጉሡ ለገሠ

ግዮን መጽሔት :-  አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ብቻ...

የኢትዮጵያ የአዲስ ዓመት ነፀብራቅ ...

  ግዮን መጽሔት :-   አዲስ ዓመት ሲቃረብ ስለ አዲስ...