ግዮን መጽሔት :- የእንቁጣጣሽ ስዕል መሳል አልወድም፡፡ እቤታችን የጎረቤት እና የዘመዶቻችን ልጆች የሚያመጧቸውን ስዕሎች ወስጄ እንድሰጥ ስለሚፈቀድልኝ ባለመሳሌ ብዙም አልቆጭም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ የእንቁጣጣሽ በዓል በመጣ ቁጥር ትዝ የሚለኝ የክርስትና አባቴ ነው፡፡
የክርስትና አባቴ ገንዘብ የማይወጣው ቆጥቋጣ ዓይነት ስለሆነ ለእርሱ የአበባ ስዕል ሰጥቶ፣ ሣንቲም ተቀብሎ ለመሄድ የሚገጥመን ፈተና ቀላል አልነበረም፡፡
በአንዱ የእንቁጣጣሽ ዕለት ልጆች ቤት ያመጡትን የአበባ ስዕሎች ይዤ በጠዋት ወደ የክርስትና አባቴ ቤት ዘንድ ሄድኩ፡፡ ብዙ የምሄድባቸው የዘመድና የጎረቤት ቤቶች ስላሉ የክርስትና አባቴ በቶሎ ሣንቲም ሰጥቶ እንዲለቀኝ እየጸለይኩ ቤቱ ገባሁ፡፡
“እንዴ! እንዴ! ማነህ አንተ?” ማንነቴን እያወቀ ሁሌ ለምን እንደሚጠይቀኝ ይገርመኛል፡፡ ቢሆንም ግን እነግረዋለሁ፡፡
“እኮ የኔው አንበሳ!?”
“አዎ!”
“እንኳን ለቅዱስ ዮሐንስ አደረሰህ?! ና እስቲ ሳመኝ?”
“እሺ!” የአበባውን ስዕል ይዤ ወደ እርሱ እጠጋለሁ፡፡
ቀረብ ስል ጉንጬን በሁለት እጆቹ ይዞ አገላብጦ ይስመኛል፡፡ ልቤ፣ “ስንት ሣንቲም ይሰጠኝ ይሆን?” በሚል ጥያቄ ስለሚያዝ የሚስመኝን ጉንጬን እንኳ አስተካክዬ አልሰጠውም፡፡
“ማነሽ ፅጌ?” ስሞኝ ሲጨርስ ትልቋን ልጅ ይጣራል፡፡
“አቤት”
“እስቲ ለእንግዳችን ዳቦ ስጪው!”
“እሺ!”
ዳቦ በሰሃን ይዛ መጥታ ትሰጠኛለች፡፡ ቶሎ ሣንቲሜን ተቀብዬ ለመሄድ ትንሷን ዳቦ መርጬ ሳነሳ፣ “እንዴ! ምነው አንተ? ያባትህ ቤት እኮ ነው፤ ፅጌ ተለቅ ያለውን ዳቦ ጨምሪለት!” ይላል፡፡ ፅጌ ትመጣና ትልቁን ዳቦ ያለ አቅሜ ታስታቅፈኛለች፡፡ በቃ መከራዬ የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ዳቦውን ካልጨረስኩ ሣንቲሙ አይሰጠኝም፡፡ ሣንቲሙ ካልተሰጠኝ ደግሞ አልሄድም፡፡ ቶሎ ካልሄድኩ ደግሞ ሌላ ቤት ለመሄድ ይረፍድብኛል፡፡
ዳቦውን ለመጨረስ ስጣደፍ ካየ፣ “ፅጌ ርቦታል መሰል፤ ጨምሪለት!” ይላል፡፡ በጣም እናደድና፣ “በቃኝ! ኧረ በቃኝ!” እላለሁ አፌ ላይ ያለውን ዳቦ በቅጡ ሳልጨርስ፡፡ ፅጌ እግዜር ይስጣትና ፍላጎቴ ገብቷት ምልስ ትላለች፡፡
ዳቦውን ጨርሼ፣ ‹ምናለ ላመጣሁት ስዕል ሣንቲም ሰጥቶኝ ቶሎ በሄድኩ› እያልኩ ስቁነጠነጥ፣ “አባትህ ደህና ነው?” ይለኛል፡፡
“ደህና ነው!” እተናደድኩ እመልሳለሁ፡፡
“እናትህስ ተሻላት?”
“አዎ! ተሽሏታል፤ መድኃኒት እየዋጠች ነው፡፡” ስናገር ፈጠን ፈጠን እያልኩ ነው፡፡
“ወንድምህስ ትምህርቱን ጨርሶ መጣ?”
“አዎ! መጥቶ ነበር፡፡ ነገ ተመልሶ ይሄዳል፡፡ የሚቀጥለው ዓመት ትምህርቱን ይጨርሳል” ስመልስ ለጠየቀኝ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ሊጠይቀኝ ይችላል ብዬ ላሰብኩት ጭምር ነው፡፡ ጥያቄውን ምነው በጨረሰ እያልኩ በሆዴ ስጸልይ፣ “ለመሆኑ ስንተኛ ክፍል ደረስክ?” የሚል ጥያቄ ያስከትላል፡፡
“አምስት!” ድምጼ መቸኮሌን ይናገር ነበር፡፡ የክርስትና አባቴ ግን ግድ የለውም፡፡
“ኧከከከ… ጎብዘሃልና እባክህ! ታዲያ ለምንድነው እየመጣህ የማትጠይቀኝ?”
“እ!?”
“እኔስ አባትህ አይደለሁም? ዘመድ አይጠየቅም?”
በፍጥነት ዳቦዬን እያላመጥኩ ዝም፡፡
“እኔ አንተን ከፅጌ እና ከትንሷ ልጄ ነጥዬ አይሃለሁ ወይ? ከወንዱ ልጄስ አሳንሼ የማይህ ይመስልሃል?”
መጨረሻውን በመናፈቅ ዝም፡፡
“‹አባቴ አምስተኛ ክፍል ደርሻለሁ፤ ደብተር መግዣ ስጠኝ፤ እስኪርብቶ ግዛልኝ!› ብትለኝ እምቢ እላለሁ?”
በሆዴ እያጉረመረኩ ጸጥ፡፡
“ሰማህ ወይ!?””
“አቤት!”
“ለአንተ ለልጄ ሣንቲም የማጣ ይመስልሃል?”
የተሰጠኝን ዳቦ ጨርሼ፣ እጁን ወደ ኪሱ የሚከትበትን ሰዓት በመናፈቅ ዓይኔን እያቁለጨለጭኩ ነው፡፡
“እኔ አባትህን ቀላል ሰው አታድርገኝ፤ እ! ይመስገነው፤ ላንተ ለልጄ የሚሆን ገንዘብ የማጣ አይደለሁም!”
በመከራ እኩን ወደ ኪሱ ከተተ፡፡ ገንዘብ ሰትቶ ሊሸኘኝ ነውና ደስ አለኝ፡፡ ድንገት እጁን ሰብሰብ አድርጎ፤
“ኧረ ለመሆኑ ያቺ እህትህስ ከቤት እንደወጣች ቀረች ወይስ ተመለሰች?”
“መጣለች፡፡ አጎቴ ይዟት መጥቷል፡፡”
“ልጇን እና ባሏን ይዛ ጎው የመጣችው?”
“አይ!”
“እና?”
“ልጇን ብቻ ነው ይዛ የመጣችው?”
“ይሁን፤ ልጇን ይዛ መመለሷም ተመስገን ነው፡፡ ባሏ እንደሆነ አለሌ ዱርዬ ነው፡፡ እርሷና ልጇ ምን ሊበሉ ነው? ኧረ እንኳን እቤቷ ገባች፤ ሆሆይ!”
“እሰይ! ጥያቄውን ጨረሰ” ብዬ በረጅሙ ስተነፍስ፣ “እንዴ! እንዴ! ያ አጎትህስ እንዲህ የጠፋው በደህናው ነው?”
“እ!?”
ማን ይሙት የአጎቴን አጠፋፍ እኔ በምን አውቃለሁ? ማንስ ሰው ብሎ ይነግረኛል? አጎቴ ትልቅ፤ ያውም የአባቴ ታላቅ፡፡ እኔ ደግሞ…
“ሁል ጊዜ እየመጣ ይጠይቃችኋል?”
“አልፎ አልፎ!”
“ይገርማል፤ ምናለ ታዲያ እኔንስ ብቅ እያለ ቢጠይቀኝ?”
“የመጣሁበትን ምክንያት ረሳው እንዴ?” እያልኩ ሳጉተመትም፣ እጁን በድጋሚ ኪሱ ከተተ፡፡ አሁንም ደስ አለኝ፡፡ ሣንቲሞች ተቃጨሉ፡፡ እንዴ ይሄን ያህል አስለፍልፎ ሣንቲም ብቻ ሊሰጠኝ ነው እንዴ? ተነጫነጭኩ፡፡ ሣንቲሞቹን አወጣቸው፡፡ ዓይኔ ከእጆቹ ጋር አብረው ተንከራተቱ፡፡ አዎ! እጁ ላይ ድፍን ስሙኒና ድፍን ሃምሳ ሣንቲም ይታዩኛል፡፡
“ማነሽ ፅጌ?”
ደግሞ ምን ሊል ነው? “እንዴ ዳቦ በቃኝ! አሁንስ ዳቦ በቃኝ! እንዴ ሌላ ቤት የማልሄድ አደረገኝ እንዴ? ዘመዴ እሱ ብቻ መሰለው እንዴ?” ንጭንጬ ለሌላ ሰው አይሰማም፡፡ ለሚመለከተኝ ሰው ግን ያስታውቅብኝ ነበር፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? የክርስትና አባቴ ግን ሊገባው አልቻለም፡፡
“ፅጌ!”
“አቤት!”
“ያንን ካፖርታ አቀብዪኝ!”
እፎይ አልኩ፡፡ የፅጌ መጠራት ለዳቦ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለኔ ብር ለመስጠት ታስቦ ጭምር በመሆኑ ተደሰትኩ፡፡ ፅጌ ካፖርት አምትታ ሰጠችው፡፡ ወዲያው የክርስታ አባቴ እጆች በካፖርቱ ኪሶች ውስጥ ገንዘብ አሰሳቸውን ተያያዙት፡፡
“እዚህ ውስጥ ዝርዝር ሣንቲም አልነበረንም ነበር እንዴ ፅጌ?”
“እኔ እንጃ ፈልገዋ!”
እንደተባለው ፈለገ፡፡ የሆኑ ሣንቲሞች አገኘ፡፡ ያሰብኩትን ድፍን ብር ባይሰጠኝም፤ ከሱሪው ኪስ ውስጥ ከተገኘው ሰባ አምስት ሣንቲም ጋር አብሮ ከሰጠኝ ያው ነው ብዬ ተፅናናሁ፡፡ … የሆነው ግን ይህ አልነበረም፡፡
“ና ወዲህ!” አለኝ በኩራት ብዙ ብር እንደሚያሸክመኝ ሁሉ፤ ወደ እርሱ ሄድኩ፡፡
“ዝርዝር ሣንቲም አጥቼ አቆየሁህ አይደል?”
“ኧረ ችግር የለም!”
“በል ይቺን ያዝ! ይኸውልህ፡፡ ስዕሉን ሌላ ቦታ ወስደህ ስትሸጠው ብዙ ሣንቲም ይሆንልሃል እሺ? ያዝ!” አዘንኩ፡፡ በጣም አዘንኩ፡፡ ክርስትና አባቴ የሰጠኝ አሥራ አምስት ሣንቲም ብቻ ነበር፡፡ ድፍን ሃምሳ ሣንቲም ላለመስጠት፣ ስሙኒ ላለመስጠት ካፖርት አስመትቶ እንደዛ መልፋቱ አበሳጨኝ፡፡ ከእጁ ላይ የመመንጨቅ ያህል ተቀብዬው ልወጣ ስል ጠራኝ፡፡
“አቤት!” ተመለስኩ ወደ ኋላ፡፡ ድንገት ተፀፅቶ ሣንቲም ቢጨምርልኝ ብዬ፡፡
“ሰማኸኝ፤ እናትህን እንደምትላት ‹እንዴት ነሽቨ ተሸለሽ ወይ? መጥቼ እጠይቅሻለሁ ስል ሳይመቸኝ ቀረ› በልልኝ፤ አደራ!”
“እሺ!” እያልኩ ወደ ውጪ ወጣሁ፡፡ እሱ ግን አልጨረሰም፡፡
“አባትህንም፣ ‹እንኳን ለቅዱስ ዮሐንስ አደረሰህ› በለው፡፡ ያ ተማሪ ወንድምህንም ሰላም በልልኝ” እኔ ከበሩ እየራቅኩ በመጣሁ ቁጥር የክርስትና አባቴ ዘለግ ያለ ድምፅ እየተከተለኝ ነው፤ “አንተ ወመኔ ምን ሆነህ ነው መጥተህ የማትጠይቀኝ በለው…”
ክርስትና አባቴ እንቁጣጣሽ በመጣ ቁጥር ይኸው ነው ባሕሪው፡፡ ሲያናድድ፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 236 መስከረም 2019 ዓ.ም
