ሩሲያ ከሶቪየት ህብረት ውድቀት ወዲህ በታሪኳ ከፍተኛ የተባለ የወታደራዊ በጀት ማጽደቋን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
ሩሲያ ከ2027 እስከ 2029 ባሉት ዓመታት ለወታደራዊ ወጪ ከ600 ቢሊዮን ዶላር በላይ መመደቧ ተገልጿል። የበጀቱ መጠን ሞስኮ የመከላከያ አቅሟንና የጦር ኃይሏን ለማጠናከር የምትሰጠውን ትኩረት ያመላክታል።
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ይህንን ከፍተኛ የወታደራዊ ወጪ ማጽደቃቸው፣ በዩክሬን ያለውን ጦርነት በቅርቡ ለማቆም ፈቃደኛ እንዳልሆኑ የሚያመላክት ምልክት ተደርጎ ተተርጉሟል።
የፖለቲካና የደህንነት ተንታኞች የወታደራዊ በጀቱ መጨመር የጦርነቱ ቀጣይነትን እንዲሁም በሩሲያና በምዕራባውያን ሀገራት መካከል ያለውን የጂኦፖለቲካዊ ውጥረት የማባባስ አደጋ እንዳለው ይገምታሉ።
የሩሲያ ውሳኔ በተለይ በአውሮፓ ሀገራት የደህንነት ስጋትን ከፍ ሊያደርግና በክልሉ የመከላከያ ወጪዎች እንዲጨምሩ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ተጠቁሟል።
