የመምህራንን ደመወዝ የሚያዘገዩ መዋቅሮች ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ተገለጸ

Date:

3ኛው ክልል አቀፍ የትምህርት ሴክተር ጉባኤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ጉባኤውን በይፋ ሲያስጀምሩ፣ ትምህርት ለሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል። በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የላቀ ደረጃ የደረሱ ሀገራት ለትምህርት ትኩረት መስጠታቸው የስኬታቸው መሠረት መሆኑንም አመልክተዋል።

ትምህርት የትናንቱን ስብራት በመጠገን፣ ዕዳን ሳይሆን ምንዳን ለትውልድ የሚያሻግር መሣሪያ መሆኑን ያነሱት አቶ ፍቅሬ፣ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የመምህራን ሚና በትምህርት ስራ ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ምቹ የሥራ አካባቢ ከመፍጠርና አቅማቸውን ከማሳደግ ባሻገር፣ የመምህራንን ደመወዝ የሚያዘገዩ መዋቅሮችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፣ በዓለም ደረጃ በሁለንተናዊ ስልጣኔ ግንባር ቀደም የነበረች ሀገር እንዴት ወደ ኋላ ቀረች የሚለውን ጥያቄ ማሰብ እንደሚገባ ገልጸዋል። ይህንን በመነሻ በማድረግ የታለመ የትምህርት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱንም አመልክተዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ከዓለም አሁን ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚወዳደር ትውልድ ካልተፈጠረ የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ጠቁመው፣ ያሉ ሀብቶችን ወደ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በትምህርት በመሆኑ ለዘርፉ ልዩ ትኩረትና ድጋፍ መስጠት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2050 የዕውቀትና ክህሎት ያለው፣ በብቃት የተካነ፣ ግብረ ገብነት ያለውና ሀገሩን የሚወድ ዜጋ የመፍጠር የትምህርት ዘርፉ ራዕይ እንዲሳካ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ጉባኤው በትምህርት የጸናች ሀገር፤ በጽናት የቆመ ትውልድ! በሚል መሪ ቃል የተጀመረ ሲሆን፣ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አዝመራ አንደሞ፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለሁለንተናዊ ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የተሻለ ለውጥ ማምጣት፣ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ለተማሪዎች ምቹ ማድረግ፣ የመምህራንን አቅም ማሳደግ፣ የትምህርት ግብዓቶችን ማሟላትና ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂ ማዘመን ላይ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል። ሆኖም ያሉ ውስንነቶችን ለመሻገር የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በጉባኤው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ተክሌ በዛብህን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችና የትምህርት ዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ኦፕሬሽን ኢትዮጵያ ለመቄዶንያ ለ4ኛ ጊዜ የአይን ህክምና አገልግሎት ሰጠ

የእስራኤል የሕክምና ተቋም የሆነው ኦፕሬሽን ኢትዮጵያ፣ ለመቄዶንያ የበጎ አድራጎት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነገ በፓርላማ ተገኝተው ማብራሪያ ይሰጣሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመጪው ሐሙስ ህዳር 17...

ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ ያስመዘገቡ ድርጅቶች ተሸለሙ

በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ዘርፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያስገኙ...

ዓለም አቀፉ ሽልማት ለጋዜጠኛ ይስሐቅ በላይ ተሰጠዉ

ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC) በ4ኛው የዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ...