በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከሱልጣን ቢን ኻሊፋ ግሩፕ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በኢንቨስትመንት ዕድሎችና በትብብር መስኮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አካሄዱ።
በግሩፑ የኻሊዲያ ሆቴል ጄነራል ማናጀር በሆኑት ሼኖል ሳሪሼን የተመራው የልዑካን ቡድን በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደረገውን የቅድመ-ኢንቨስትመንት ምልከታና የሥራ ጉብኝት አስመልክቶ ሰፊ ገለጻ ቀርቧል።
በጉብኝታቸው ወቅት በኢትዮጵያ እጅግ አበረታችና ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር መመልከታቸውን የገለጹት የሥራ ኃላፊዎቹ፣ በተለይም በአገልግሎት ዘርፍ አዳዲስ ግዙፍ ሆቴሎችን ለመገንባትም ሆነ ነባር ሆቴሎችን ተረክቦ በማዘመን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ የንግድ ዕድሎች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
አክለውም የነበረውን የምልከታ ጉብኝት ተከትሎ ኩባንያቸው አሁን ላይ ወደ ተጨባጭ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ ለመግባት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
አምባሳደር ዶ/ር ጀማል በከር በበኩላቸው ልዑኩ በኢትዮጵያ ለነበረው ፍሬያማ ቆይታና ለሰጠው በጎ ምላሽ ምስጋና አቅርበዋል።
አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶች ማዕከል እየሆነች መምጣቷን የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ በተለይም ኢትዮጵያ የ32ኛውን የዓለም አቀፍ የኮፕ (COP 32) የአየር ንብረት ጉባኤን ለማዘጋጀት መመረጧ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ዘላቂና ትልቅ የንግድ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ሱልጣን ቢን ኻሊፋ ግሩፕ ወደ ተጨባጭ ኢንቨስትመንት በሚገባበት ጊዜም ሆነ በቀጣይ የሥራ እንቅስቃሴዎቹ የኢፌዲሪ ኤምባሲ አስፈላጊውን ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠውላቸዋል።
