በህንድ ውቅያኖስ ላይ በደረሰ አደጋ 250 ስደተኞች የደረሱበት አልታወቀም

Date:


የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከባንግላዴሽ ወደ ማሌዥያ የተጓዙ 2መቶ50 የሚጠጉ የሮሂንጋ እና የባንግላዴሽ ስደተኞች የጫነቻቸው ጀልባ በአንዳማን ባሕር ላይ በመገልበጧ ምክንያት የደረሱበት ሳይታወቅ ቀርቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ትናንት ባወጡት የጋራ መግለጫ፤አደጋው የተከሰተው በከባድ ነፋስ እና በጀልባዋ ላይ በተጫነው ከመጠን ያለፈ የሰው ብዛት መሆኑን አረጋግጠዋል።

ጉዞው የተጀመረው ሚያዝያ 4 ቀን ሲሆን፤አብዛኞቹ ተጓዦች በምያንማር ከደረሰባቸው ጭፍጨፋ አምልጠው በባንግላዴሽ የካምፕ ሕይወት ሲገፉ የቆዩ የሮሂንጋ ተወላጆች ናቸው።

እንደ አይን እማኞች ምስክርነት ከሆነ፤ሚያዝያ 7 ቀን ጀልባዋ በማዕበል ተመታ ስትሰምጥ ተጓዦቹ ለሁለት ቀናት ያህል በባሕር ላይ በበርሜሎች እና በስብርባሪ እንጨቶች ተንጠልጥለው ለመቆየት ተገደዋል።

በሚያዝያ 11 ቀን ሌሊት፣ ወደ ኢንዶኔዥያ በጉዞ ላይ የነበረችው ‹‹ሜግና ፕራይድ›› የተባለች የነዳጅ ጫኝ መርከብ ዘጠኝ ሰዎችን በሕይወት ማዳን የቻለች ቢሆንም ቀሪዎቹ 250 ሰዎች ግን እስከ አሁንም አልተገኙም።

የባንግላዴሽ የባሕር ጠረፍ ጥበቃ ባልደረቦች እንደሚሉት የጀልባዋም ሆነ የሌሎቹ ተጓዦች ፍንጭ እስካሁን አልተገኘም።

መፍትሔው የፖለቲካ እንጂ የሰብዓዊ ዕርዳታ ብቻ ባለመሆኑ ይህ አደጋ በክልሉ ለዓመታት የዘለቀውን የሮሂንጋ ስደተኞች ቀውስ ዳግም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት እንዲስብ አድርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሀገራት ለስደተኞች የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ እንዲቀጥሉ ከማሳሰብ ባለፈ፣ በምያንማር ውስጥ ለስደተኞቹ መፈናቀል ምክንያት የሆኑ መሠረታዊ ችግሮች እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2025 መጀመሪያ ላይ ማሌዥያ እና ኢንዶኔዥያ ስደተኞችን የጫኑ ጀልባዎችን ወደ ባሕር መመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም ስደተኞቹን ይበልጥ ለአደጋ እያጋለጣቸው መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየገለጹ ነው።

ሊዲያ ደሳለኝ

ሚያዚያ 07/2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ ለተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች የሚጫወቱ ወንድማማቾች

የ2026 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ምርጥ ተጫዋቾችን...

ኢንፊኒቲ ለቤትና ለመኪና መግዣ ብድር እየሰጠ እንደሚገኝ አስታወቀ

ኢንፊኒቲ ኃላፊነቱ የተወሠነ መሠረታዊ የቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ...

የአዲሱ የወንጀል ህግ ስነ-ስርዓት የእርማት ስራዎች ሳይጠናቀቁ በሥራ ላይ እየዋለ ነው

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላለፉት 64 ዓመታት...

ናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውጭ ኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ አገኘ

​የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ታሪክ ለመጀመሪያ...