3ኛው “የአዕላፋት ዝማሬ” መርኃግብር ታኅሳስ 28፣ 2018 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ እና በድሬደዋ በለገሀር አደባባይ እንደሚከናወን አዘጋጁ የጃንደረባው ትውልድ አጠቃላይ ማኅበር (ኢጃት) በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ባለፉት ሁለት መርሐግብራት ከተሳተፉ ምዕመናን በተሰበሰበ ዳታ ላይ በተሰራ የዳሰሳ ጥናት መሰረት በ3ኛው ዙር በርካታ ማስተካከያዎች መደረጉን አንስቷል።
ለምን በመስቀል አደባባይ እንዲካሄድ ተወሰነ ?
ማኅበሩ በዳሰሳ ጥናቱ በዋነኝነት ” የአዕላፋት ዝማሬ የሚካሄድበት ቦታ ጥበትና ከልክ ያለፈ መጨናነቅ” በቅሬታ መነሳቱን ገልጾ “ሰዎች ራሳቸውን እስከመሳትና ብዙ ነጠላዎች በጠዋፍ እስከመቃጠል በመድረሱ” ቦታውን ለመቀየር በዋና ምክንያትነት አንስቷል።
በተጨማሪም ” መስቀል አደባባይ እንዲከበር እንፈልጋለን የሚለው የመጀመሪያው ዓመት ጥያቄ መደጋገሙ ” ሌላው በምክንያትነት የተነሳ ጉዳይ መሆኑን ማኅበሩ ጠቅሷል።
3ኛው ዙር የአዕላፋት ዝማሬ ስንት ሰዓት ተጀምሮ ስንት ሰዓት ይጠናቀቃል ?
” መርሐግብሩ በመሃርነ አብ ጸሎት፤ በቅዱስ ፖትሪያሪኩ እና በብፁዓን አበው ሊቀ ጳጳሳት ጸሎተ ወንጌልና ጸሎተ ኪዳን ከቀኑ 9:00 ሰዓት ይከፈታል።
ከአባቶች ጸሎት ቃለ ምዕዳን እና ዘማሬ ውጪ ምንም አይነት የክብር እንግዶች ንግግር፣ ገቢ ማሰባሰቢያ እና ሌሎች መልዕክቶች የሚተላለፉበት መድረክ ባለመሆኑ በዚህም ዓመት ይህንን መንፈሳዊ ይዘት ይዘን እናስቀጥላለን።
በዕለቱ 30 መዝሙራት ይዘመራሉ።
መርሐግብሩ ከምሽቱ 1:30 ላይ ይጠናቀቃል። በጊዜ የሚጠናቀቅበትም ምክንያት ያለፉትን ተግዳሮቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ምዕመናን እንዲያስቀድሱ ለማድረግ ነው ” ሲል ማኅበሩ አስረድቷል።
ፈቃድን በተመለከተ ምን ተባለ ?
የአዕላፋት ዝማሬን በመስቀል አደባባይ ለማከናወን ” አስፈላጊ ሰነድ ተሟልቶ አስፈላገው ሰነድ ተገኝቷል ” ያለው ኢጃት ከመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ቀድሞ ለከተማ አስተዳደሩ መላኩን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ ዙር መርሐግብራት በሰላም በመጠናቀቁ ” የከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት እና የከተማው ጸጥታ ቢሮ የአዕላፋት ዝማሬ በመስቀል አደባባይ ይካሄድ የሚለውን በበጎ እንዲመለከተው አግዟል ” ብሏል።
ምዕመናን፥ ቀኑ ሲቀርብ የከተማው የጸጥታ አካል ለሚሰጠው ዝርዝር መመሪያ እና በዕለቱ ሁነቱን በሰላም ለማጠናቀቅ ለሚደረገው ፍተሻ በተለመደው መንፈሳዊ ትዕግሥት እንዲተባበሩ ጠይቋል።
አባቶች የበዓሉን አከባበር በተመለከተ ተጨማሪ መግለጫ እና አባታዊ መልዕክት የሚያስተላልፉም ጠቁሟል።
” እድሜያቸው 15 ዓመት በታች የሆኑትን ይዛችሁ ባለመምጣት እንድትተባበሩን ” ሲል ማኅበሩ የጠየቀ ሲሆን ቀደም ብሎ እስከ ታኅሳስ 23 ድረስ በግዮን ግራውንድስ በአዕላፋት ሳምንት የህጻናት የአዕላፋት የዝማሬ መርሐግብር መዘጋጀቱን ገልጿል።
ለነፍሰ ጥሩችና አካል ጉዳተኞች የተዘጋጀ ልዩ ስፍራ ስላለ ለአስተባባሪዎች በማሳወቅ ባታ ማግኘት ይቻላል ብሏል። በተጨማሪም ክሊኒኮች፣ ተንቀሳቃሽ ሽንት ቤቶች እና አምቡላንስ መዘጋጀቱን ጠቁሟል።
@tikvahethiopia
