በአዲስ አበባ የታክስ ዕዳ ምህረት አሰጣጥን የሚያስተዳድር አዲስ ረቂቅ መመሪያ ወጣ

Date:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ፣ በተለያዩ ከግብር ከፋዮች አቅም በላይ በሆኑ ሁኔታዎች ምክንያት የተከማቸ የታክስ ዕዳ ለማስተናገድ የሚያግዝ አዲስ ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅቷል።

መመሪያው በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በንግድ ኪሳራ፣ በከባድ ህመምና በሌሎች ከአቅም በላይ በሆኑ ሁኔታዎች የታክስ ግዴታቸውን መወጣት ላልቻሉ ግብር ከፋዮች የዕዳ ምህረት የሚሰጥበትን ሂደት በግልጽ ለመወሰን ያለመ ነው።

በረቂቅ መመሪያው መሠረት ምህረቱ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ግብር ከፋዮች ለምህረት ጥያቄያቸው የሚያቀርቡትን ምክንያት በሕጋዊ ሰነዶች ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።

ለምሳሌ፦

• በተፈጥሮ አደጋ፦ በጎርፍ፣ በመሬት መንሸራተት ወይም በእሳት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ግብር ከፋዮች ከሚመለከታቸው ተቋማት የተሰጠ የጉዳት ማረጋገጫ ማቅረብ አለባቸው።

• በንግድ ኪሳራ፦ ድርጅቶች የፋይናንስ አቅም ማነስን የሚያሳይ በሕጋዊ ፈቃድ ባለው ባለሙያ የተረጋገጠ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

• በጤና ችግር፦ ከባድ ህመም ወይም የአካል ጉዳት ሲያጋጥም የሕክምና ማረጋገጫ፣ የወጪ ሰነዶችና ከወረዳ የተሰጠ ደብዳቤ ያስፈልጋሉ።

የምህረት ጥያቄ የሚያቀርብ ማንኛውም ግብር ከፋይ በመጀመሪያ በገቢዎች ቢሮ የቴክኒክ ግምገማ ማለፍና ለምህረት ብቁ መሆኑን የሚያረጋግጥ የድጋፍ ደብዳቤ ማግኘት አለበት።

ከዚህ በተጨማሪ የምህረት ጥያቄዎችን ለመመርመር በቢሮው ኃላፊ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ይሰየማል። ኮሚቴው ጥያቄው ከቀረበ በ15 ቀናት ውስጥ ግምገማውን አጠናቆ የውሳኔ ሐሳቡን ያቀርባል። የቢሮው ኃላፊም ሐሳቡ ከደረሰው በኋላ በ5 ቀናት ውስጥ ያጸድቃል፣ ያሻሽላል ወይም ይሽራል።

ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የምህረት ጥያቄዎች ግን በፋይናንስ ቢሮው ከተጣሩ በኋላ ለመጨረሻ ውሳኔ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ይቀርባሉ።

ረቂቅ መመሪያው በሕገወጥ መንገድ የታክስ ስወራ በፈጸሙ ግብር ከፋዮች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆንም ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ረቂቅ መመሪያው ግብዓት በመሰብሰብ ላይ ሲሆን በሕጋዊ ሂደቱ መሠረት ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ ይሆናል።

ማስታወሻ፦ ይህ ገና ረቂቅ መመሪያ እንጂ የጸደቀና ተግባራዊ የሆነ ሕግ አይደለም።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እግዚአብሔር የሰጠኝን ተልዕኮዎች ፈጽሜያለሁ የአዛዥነት ዘመኔ እያበቃ ነው

የኡጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች አዛዥ (CDF) ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ከወታደራዊ...

አሐዱ ባንክ 1ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ባንኩ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር...

በጋምቤላ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ...

ፍልውሃ እና ሶደሬ!

ከሐዉለት አህመድ በቀደም ከብዙ ዓመታት በኋላ የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት ሔጄ...