በሩሲያ ደቡብ ምዕራብ ሳይቤሪያ በሚገኘው ኬሜሮቮ ግዛት የወታደራዊ ማጓጓዣ አውሮፕላን ተከስክሶ በውስጡ የነበሩ 19 ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸው ማለፉን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
አደጋው በኬሜሮቮ ግዛት ያጉኖቮ በተባለች መንደር አቅራቢያ በሰው በማይኖርበት አካባቢ የደረሰ ሲሆን፣ የተከሰከሰው አንቶኖቭ ኤን-12 የተሰኘ ወታደራዊ ማጓጓዣ አውሮፕላን ነው።
በአደጋው የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 19 ሰዎች በሙሉ ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በመጀመሪያ ደረጃ መረጃው አውሮፕላኑ በመደበኛ በረራ ላይ እያለ በገጠመው የቴክኒክ ብልሽት ምክንያት እንደተከሰከሰ ጠቁሟል።
የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በስፍራው በመድረስ እሳቱን በቁጥጥር ሥር ያዋሉ ሲሆን፣ የአደጋውን ትክክለኛ መንስኤ ለማጣራት ልዩ መርማሪ ቡድን ወደ ቦታው መላኩ ተገልጿል።
