በየእለቱ ለጉብኝት ወደ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፖርክ የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ፓርኩ ህገወጥ ተግባራት የሚከናወንበት መሆኑን የፓርኩ ፅ/ቤት አስታውቋል ።
የፓርኩ ፅ/ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ላቀው መልካሙ እንደተናገሩት በፓርኩ ውስጥ ከህገወጥ ሰፈራ ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በተደረገው ጥረት እንዲህ ያለው ድርጊት አሁን ላይ ቀንሷል።
ይሁን እንጂ ሰዎች ከብቶቻቸውንና የቤት እንስሳቶቻቸውን ወደ ፓርኩ በማስገባት ስፍራውን ለግጦሽ እንዲውል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በፓርኩ ውስጥ ቀደም ካሉት ጊዜያቶች አንስቶ የሰፈሩ ከ2መቶ በላይ አባወራዎች እንዳሉ የተናገሩት ተወካይ ኃላፊው በቦታው ላይ ምንም አይነት ጫና እንዳያሳድሩ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጨምረው ገልፀዋል።
ነገር ግን የፓርኩን ደህንነት ሙሉ ለሙሉ ለመጠበቅ እና ለጉዳዮ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በሚመለከተው አካል በኩል ወደ ሌላ ቦታ መዛወር እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ላቀው ገልፀው። ይህን ለመከላከል ለማህበረሰቡ እየተደረገ ያለው የግንዛቤ መፍጠር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የፓርኩ አዋሳኝ በሆነው በጃናሞራ ወረዳ በሚገኙ አጥገባ እና ድብል ቀበሌዎች ከአጋር አካለት ጋር በመቀናጀት ለ750 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማሳደግ ስራ መከናወኑ ተገልጿል።
ለዚህ አላማ በተዘጋጀው መድረክ ፓርኩ ተጠብቆ ከቆየ ለቱሪስት መዳረሻነት በሚኖረው ፋይዳ እና ከዋልያ ጋር ተያይዞ የሚኖረውን ሀይማኖታዊ ዳራን በማንሳት ውይይት ተካሂዷል።
