በሰሜን ጎንደር ዞን በየወሩ ከ30 በላይ አዳዲስ የኤችአይቪ ተያዦች እየተመዘገቡ መሆኑን የዞኑ ኤችአይቪ ኦፊሰር አቶ ሰለሞን መኮንን ገልጸዋል።
በዞኑ የኤችአይቪ ስርጭት እየጨመረ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በማይጸምሪና ዲማ ወረዳዎች ሳይጨምር በቀሩት የዞኑ አካባቢዎች ከ2 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ከኤችአይቪ ጋር እየኖሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ከስርጭቱ መጨመር ጋር ተያይዞ ከተጠቀሱት ምክንያቶች መካከል፣ ማህበረሰቡ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ ትኩረት ቢያደርግም ከኤችአይቪ መከላከል አንጻር በቂ ግንዛቤ አለመኖሩ ተጠቅሷል።
ይህ የግንዛቤ ክፍተት በተለይ አፍላ ወጣቶችን ለቫይረሱ ተጋላጭ እያደረገ መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። በዞኑ የኤችአይቪ ስርጭት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
ስርጭቱን ለመቀነስ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን ማጠናከርና የኤችአይቪ ምርመራ አገልግሎቶችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ አቶ ሰለሞን መኮንን አሳስበዋል።
