በአዲስ አበባ #በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዛሬ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ረፋድ ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን የከተማዋ የትራፊክ መምሪያ አስታወቀ፤ ከሟቾቹ መካከል የሶስት ዓመት ዕድሜ ያለው ህፃን ይገኝበታል ብሏል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ አባሳሙኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባጋጠመ የተሽከርካሪ አደጋ ህይወታቸው ካለፈው በተጨማሪ በስምንት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ከከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አደጋው ሊከሰት የቻለው ከሃይሌ ጋርመንት ወደ ዩኒሳ አደባባይ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-78979 ኢት የሆነ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አውቶቡስ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-04273 ኢት ከሆነ ሌላ ከባድ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ እና መንገድ ስቶ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ በመግባቱ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል።
አውቶቡሱ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ከገባ በኋላ ከዩኒሳ አደባባይ ወደ ሃይሌ ጋርመንት ሲጓዝ ከነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-77970 ኦሮ ከሆነ ዶልፊን ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ በዶልፊኑ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች መካከል አሽከርካሪውን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው ላይ የቆመ እና በጉዞ ላይ የነበረ ሌሎች ሁለት ተሽከርካሪዎች በአውቶቡሱ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፤ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
