“ ግዕዝ የሞተ ቋንቋ ነው ” – በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)
“ ግዕዝ የሞተ ቋንቋ አይደለም ! ” – የወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህርመምህር ይባቤ ፈቀደ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የግዕዝ ቋንቋ ትምህርትን ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ልሰጥ ነው ማለቱን የደሴ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት እንደሚቃወም ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ከዚያ በኋላ ስለጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያው በርካታ ክርክሮች እየተንሸራሸሩ ሲሆን፣ ለአብነትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ትምህርትና ሥና ጽሑፍ መምህርና ደራሲ በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ለቢቢሲ በሰጡት ቃል፣ “ ግዕዝ የሞተ ቋንቋ ነው ፤ ይህን ቋንቋ እንደ አንድ የትምህትት አይነት ከሶስተኛ ክፍል ጀምሮ መሰጠቱ እርባና የለውም ” ብለዋል፡፡
“ አንድ ቋንቋ የአፍ መፍቻ ተናጋሪ ከሌለው እና ከ25 ሺህ በታች ተናጋሪ ካለው ሞቷል ይባላል። ይህን የሞተ ቋንቋ ከታች ከፍል ጀምሮ መስጠት የተማሪዎችን ጊዜ ማጥፋት ነው ” ብለዋል።
ቋንቋን የመማር ወሳኝ ዓላማ ለተግባቦት እና ሕይወትን ለመምራት እንደሆነ የሚናገሩት መምህር በድሉ ግእዝ ለተግባቦትም ሆነ ሕይወትን ለመምራት አሁን ላይ ጥቅም የለውም ብለዋል።
ሆኖም የግእዝ ቋንቋ ጭራሽኑ በትምህርት መልክ መሰጠት የለበትም ብለዋል።
የግእዝ ቋንቋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በጀርመን እና በፈረንሳይ ውስጥ ይሰጣል ያሉ ሲሆን ቋንቋው የሚሰጠው በግእዝ ቋንቋ ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ትምህርቱ ይሰጥ ከተባለ መሰጠት ያለበት ከ9 ክፍል ጀምሮ ወይም ለአንትሮፖሎጂ፣ ለታሪክ እና ለቋንቋ ጥናት ፍላጎት ላላቸው የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች እንዲሆን መክረዋል።
ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን የሰጡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ግዕዝ ቋንቋ እና ሥነ ፅሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር ይባቤ ፈቀደ፣ “ ግዕዝ የሞተ ቋንቋ ነው የሚሉ ሰዎች የተሳሳቱ ናቸው። አረብኛም ግዕዝም የሴሜቲክ ቋንቋዎች ናቸው፡፡ እየተነሳ ያለው ተቋውሞ ከግንዛቤ እጥረት የመነጨ ነው ” ይላሉ፡፡
“ ይህንን ተቃውሞ የሚያራምዱ ሰዎች ጉዳዩ ኃይማኖት የማስፋፋት ጽንሰ ሀሳብ መስሎ ተሰምቷቸዋል ” ያሉት አቶ ይባቤ፣ “ ፈጣሪ በቋንቋ አይወሰንም፤ ቋንቋ ኃይማኖት አይደለም መሳሪያ ነው ” ብለዋል፡፡
“ ቋንቋ መቼም ቢሆን ኃይማኖት ሆኖ አያውቅም፡፡ መረጃዎችን ማሳየት እችላለሁ በግዕዝ የተጻፉ ብዙ የእስልምና እምነት ፅሑፎች አሉ፡፡ በአረቢክ የተጻፉ ብዙ የኦርቶዶክስ ፅሑፎች አሉ ” ነው ያሉት፡፡
“ ተቃውሞ ያስነሱ ሰዎች ቆም ብለው ይዩት፡፡ ቋንቋ ቋንቋ ነው አላህ ይሴባህ፣ እግዚአብሔር ይሴባህ ብሎ ማመሰገን ይቻላል ” ያሉት የግዕዝ መምህሩ፣ “ፍትህ ነገስት፣ ክብረ ነገስት ከአረብኛ የተተረጎሙ ናቸው” ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
“ በጥልቀት ካለመገንዘብ የተነሳ እንጅ ግዕዝ የሞተ ቋንቋ አይደለም፡፡ ብዙ ተናጋሪ አለው፤ በኛ ደረጃ እንኳ ከተመረቁት ውጭ በሬጉላር ሦስት ባች ተማሪዎች አሉን ” ብለዋል።
“ አንድ ቋንቋ ሞተ የሚባለው የሚጽፍው፣ የሚያነበውና የሚናገረው ሲያጣ ነው፡፡ ግዕዝ ግን በዚያ ደረጃ አይደለም በሰፊው የሚናገረው፣ የሚጸፈውና የሚያነበው አለው ” ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ጥቅሙን በተመለከተ የግዕዝ መምህሩ ምን አሉ ?
“ ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ከ25 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ግዕዝን በስርዓተ ትምህርታቸው አካተው እየሰጡ ነው፡፡
ግዕዝ በሀገር ደረጃም በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ነው፡፡ ጥቅም አለው፡፡ ለምሳሌ ማዕድን የት፣ የት እንደሚገኝ ጠቋሚ አቅጣጫዎች በግዕዝ መጻሕፍት ተጽፈዋል፣ ኢትዮጵያ ምን አይነት የምህንድስና ጥበብ እንዳላት ተሰንደውበታል፡፡
ሀገሪቱ አንድነቷንና ነጻነቷን ጠብቃ እንድትኖር የቀድሞ ነገስታት ያስተዳድሩበት የነበረው የአስተዳደር ስልት በግዕዘ ውስጥ ተከትቦ ይገኛል፡፡ ስለዚህ እነዚህና መሰል ጥቅሞች እንዳሉት ልብ ልንል ይገባል ” ብለዋል፡፡
TikvahEthiopia
