ትራምፕ “የኢራን ኒውክሌር ይዞታዎች አልወደሙም” ሲል ፔንታጎን ያወጣውን ግምገማ ውድቅ አደረጉ

Date:

አሜሪካ ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት “የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን አላወደመም” ሲል የአሜሪካ መከላከያ ማዕከል (ፔንታጎን) የደህንነት ግምገማ አሳይቷል።

ቅድመ ግምገማው ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምናልባትም በወራት ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል ማመላከቱን የአገሪቱ የመከላከያ ደህንነት ኤጀንሲ ግምገማን የሚያውቁ ምንጮች ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

ዋይት ሃውስ በበኩሉ “ይህ ፍጹም የተሳሳተ ግምገማ በማይረባ የደህንነት ማህበረሰብ ሾልኮ የወጣ ነው” ሲል ግምገማውን ውድቅ አድርጎታል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ “የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል” በማለት በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተው፤ “በታሪክ ውስጥ ስኬታማ ከሆኑ ወታደራዊ ጥቃቶች መካከል አንዱ የሆነውን ለማዋረድ በሚዲያዎች የሚደረግ ሙከራ ነው” ሲሉም ከሰዋል።

የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በበኩላቸው፤ የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች ጥቃት ላይ የአሜሪካ መከላከያ (ፔንታጎን) የደህንነት ግምገማ ሾልኮ መውጣቱን “የአገር ክህደት” ሲሉ ጠርተውታል።

“በጣም አሳፋሪ ነው፤ የአገር ክህደት ነው። ምርመራ ተካሂዶ ጥፋተኛው አካል ተጠያቂ ሊደረግ ይገባል” ሲሉ ለፎክስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ልዩ መልዕክተኛው አገራቸው በሶስቱ የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎች ላይ የፈጸመችውን ጥቃቶች ግምገማ ሪፖርቶች ማንበባቸውን የገለጹም ሲሆን፤ “ሙሉ በሙሉ ስለመውደማቸው ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛቸው ከፎክስ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በመቀነጫጨብ በትሩዝ ሶሻል ማህበራዊ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።

አሜሪካ ፎርዶ፣ ናታንዝ እና ኢስፋን የተሰኙ ሶስት የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎችን 61 ሜትር ወደ መሬት ዘልቆ መግባት በሚችሉ “በንከር በስተር” በተሰኙ ቦምቦች ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል።

ነገር ግን የፔንታጎን የደህንነት ግምገማን የሚያውቁ ምንጮች በበኩላቸው፤ የኢራን ማብላያዎች በአብዛኛው እንዳልተነኩ እና የጥቃቱ ተጽእኖ ከመሬት በላይ ባለው ብቻ የተወሰነ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱ ኒውክሌር ይዞታዎች መግቢያዎች ተዘግተው እንደነበር የጠቀሰው ግምገማው፣ “አንዳንድ መሰረተ ልማቶች ቢወድሙም ወይም ቢጎዱም፤ ነገር ግን ከመሬት ስር ያሉት አብዛኛዎቹ ይዞታዎች ከፍንዳታው ቃጠሎ አምልጠዋል” ብሏል።

እኚህ ማንነታቸው ያልተገለጹ ምንጮች ለአሜሪካ ሚዲያ እንደተናገሩት፤ ጥቃቱ ኢራንን በወራት ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል መገመቱን ገልጸዋል።

ኢራን ማንኛውም የኒውክሌር መርሃ ግብሯን እንደገና ለመጀመር ቁፋሮ እንዲሁም አንዳንድ ጥገናዎች ምን ያህል ይወስዳሉ? በሚለው ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚችልም ምንጮቹ አስረድተዋል።

ኢራን ከጥቃቱ በፊት የተወሰነውን በለጸገው የዩራኒየም ክምችቷን ወደ ሌሎች ስፍራዎች አዛውራም እንደነበር የደህንነት ግምገማው ማየቱን እኚሁ ምንጮች አረጋግጠዋል።

የኢራን ከመሬት በታች የተገነቡ የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን መድረስ የሚችለው የአሜሪካው 14 ሺሕ ኪሎግራም የሚመዝነው ‘በንከር በስተር’ እንደሆነ ይታመናል። ኢራን ሁሉም የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ ዓላማ እንደሆነ በተደጋጋሚ ስታሳውቅ ቆይታለች።

ጥቃቱን ተከትሎ በነበሩት ሰዓታት የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን በይዞታዎቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመገምገም ጊዜ ይወስዳል የሚል አስተያየት ሰጥተው እንደነበርም ይታወሳል።

የሳተላይት ምስሎች ዋነኛው በሚባለው የፎርዶ ኒውክሌር ማብላያ ሁለት መግቢያዎች ዙሪያ ስድስት አዳዲስ ጉድጓዶች እንዲሁም ግራጫ ብናኝ እና ፍርስራሾችን አሳይተዋል።

ሆኖም ከመሬት በታች ከ80-90 ሜትር ጥልቀት ላይ በሚገኘው በዚህ የኒውክሌር ማብላያ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ እነዚህ የሳተላይት ምስሎች አለማሳየታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

የኢራን የመንግሥታዊ ሚዲያ ምክትል የፖለቲካ ዳይሬክተር ሃሰን አብደኒ፤ አሜሪካ ጥቃት ያደረሰችባቸው ሶስቱ የኒውክሌር ይዞታዎች፣ ከጥቃቱ ቀድሞ ክምችታቸው እንዲዛወር መደረጉን መናገራቸውም ይታወሳል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ፈንታዬ በላይነህ የቦስተን ግማሽ ማራቶንን ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ አሸነፈች

በ2026 የቦስተን ግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት...

ስፖርቲንግ ሊዝበን ለክርስቲያኖ ሮናልዶ እናት እውቅና ሰጠ

የፖርቹጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበን ለክርስቲያኖ ሮናልዶ እናት ማሪያ ዶሎሬስ...

በአዲስ አበባ የታክስ ዕዳ ምህረት አሰጣጥን የሚያስተዳድር አዲስ ረቂቅ መመሪያ ወጣ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ፣ በተለያዩ ከግብር ከፋዮች...