በኢትዮጵያ አንጋፋ ከሆኑት የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ናይል ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር በ2017 በጀት ዓመት 560.5 ሚሊዮን ብር ከታክስ በፊት ትርፍ በማግኘት በኩባንያው ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን የትርፍ መዝገብ አስመዝግቧል።
ሆኖም የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች ማደግና የገበያ ተግዳሮቶች ለአንድ አክሲዮን የሚከፈለውን የትርፍ ድርሻ (EPS) በ5 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርገውታል።
ኩባንያው ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት፣ የተመዘገበው የ560.5 ሚሊዮን ብር ትርፍ ካለፈው ዓመት የ480.6 ሚሊዮን ብር አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ16.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
ይህ ውጤት የተገኘው ኩባንያው በመደበኛው የኢንሹራንስ አገልግሎትና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ባከናወናቸው ስልታዊ ተግባራት መሆኑ ተገልጿል።
ይሁን እንጂ የኩባንያው አጠቃላይ ትርፍ ቢያድግም፣ የአንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ (Earnings Per Share) ካለፈው ዓመት ከነበረበት 439 ብር ወደ 417 ብር ወርዷል። ለዚህም በዋናነት የተጠቀሰው የቢሮ ኪራይ፣ የነዳጅ፣ የጥገናና የፋይናንስ ወጪዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸው ነው።
የቦርድ ሰብሳቢው አቶ መሐሪ ዓለማየሁ እንደገለጹት፣ በባንኮች ላይ የተጣለው የ24 በመቶ የብድር ጣሪያ ከብድር ጋር ተያይዘው የሚሸጡ የኢንሹራንስ ምርቶች ፍላጎት እንዲቀንስ አድርጓል።
