አሜሪካ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ300,000 በላይ ቪዛዎችን መሰረዟን አስታወቀች
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከ300,000 በላይ ቪዛዎችን መሰረዛቸውን አስተዳደራቸው አስታወቀ።የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ300,000 በላይ ቪዛዎችን መሰረዙን ማክሰኞ ዕለት ያስታወቀው የፌዴራል መንግሥቱ በስደተኞች ላይ የሚያደርገውን ሰፊ የቁጥጥር እርምጃ አጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው።
ይህ ቁጥር ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ቪዛ የመሰረዝ ሂደቱ በከፍተኛ ሁኔታ መፋጠኑን ያሳያል።
“ከ300,000 በላይ ቪዛዎች ተሰርዘዋል፤ ቁጥሩም እየጨመረ ነው። ለቪዛ ባለቤቶች ያለን መልዕክት ቀላል ነው፤ ሕጎቻችንን አክብሩ፤ አለበለዚያ ወደ አሜሪካ የመጓዝ መብታችሁን ታጣላችሁ” ሲሉ የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቆንስላ ጉዳዮች ረዳት ጸኃፊ ሞራ ናምዳር በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
“ለፕሬዚዳት ትራምፕ እና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ አገራችንን እና ሕዝባችንን መጠበቅ ዛሬም ሁሌም ቀዳሚው ነገር ነው” ሲሉም አክለዋል።
ኃላፊዋ በገጻቸው ላይ ዋይት ሐውስ “የትራምፕ አስተዳደር በታሪክ ከነበሩ አስተዳደሮች ሁሉ በበለጠ ፍጥነት እና ብዛት ቪዛዎችን ሰርዟል” በማለት የለጠፈውን መልዕክት አጋርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ቶሚ ፒጎት በኤክስ ገጻቸው ላይ ቪዛቸው የተሰረዘው ውጭ ዜጎች በሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ለይ የተሳተፉ ወይም ለብሔራዊ ደህንነት አደጋ የደቀኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
“እዚህ ቪዛ ኖሯቸው ሕግን የሚጥሱ፣ ማጭበርበር የሚፈጽሙ ወይም ብሔራዊ ደህንነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ የውጭ ዜጎችን በፍጹም አንታገስም” ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመርያ ላይ ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያሳየው የትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ ከ175 ሺህ በላይ ቪዛዎች መሰረዛቸውን አስታውቆ ነበር።
አሁን ይፋ የሆነው ቁጥር በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቪዛዎች መሰረዛቸውን የሚያሳይ ነው።
ትራምፕ ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞችን ወደ መጡበት አገር ማባረር የአገር ውስጥ ደህንነትን ለማሻሻል ዓላማ ያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
