ቶተንሀም ሆትስፐርን ከሊቨርፑልን ያገናኘው የ2019 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በማድሪድ ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስቴዲየም ሊደረግ ሰዓታቶች ብቻ ይቀራሉ፡፡ በዚህ ሰአት አንድ አስደንጋጭ ዜና ተሰማ፡፡ በማድሪድ ዋና ከተማ::
የሚደረገውን ጨዋታ ለመታደም ወደ ቦታው ሲያመራ የነበረው የቀድሞው የአርሰናል አማካይ ጆሴ አንቶኒዮ ሬስ በመኪና አደጋ ህይቱ አለፈ፡፡
ለሁለቱም የማድሪድ ከተማ ክለቦች አትሌቲኮ እና ማድሪድ ተጫውቶ ያሳለፈው አማካይ በሰአት 116 ኪሎ ሜትር ማሽከርከሩ ለአደጋውም ለህልፈቱም ምክንያት እንደነበር ፖሊስ ይፋ አደረገ፡፡
ከ6 አመት በኋላም በዚያው በስፔን የዲየጎ ዦታ ህይዎት በተመሳሳይ መኪና አደጋ ተነጠቀ፡፡
የሊቨርፑሉ አጥቁ በስፔን ዛሞራ ሴርናዲላ በምትባል ቦታ ከታናሽ ወንድሙ ጋር በሚጓዙበት ሰአት ነው አደጋው ያጋጠማቸው፡፡ ለመሆኑ የ28 አመቱ ፖርቹጋላዊ ስፔን እንዴት ተገኝ ?
የሊቨርፑል የቅድመ ውድድር ዝግጅት በመጭው ማክሰኞ የሚጀመር በመሆኑ ሁሉም ተጫዋቾች እንዲገኙ አርን ስሎት ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
ዲየጎ ዦታም በተባለው ቀን እንግሊዝ ለመድረስ መነሻውን ከትውልድ ቦታው ፖርቶ አድርጎ ወደ
ስፔን በግል መኪናው መጓዝ ይጀምራል፡፡
ለመሆኑ ከፖርቹጋል ወደ እንግሊዝ ለመጓዝ ስለምን የየብስ ትራንስፖርትን መረጠ ካላችሁ መልሱ ይሄ ነው፡፡
ዦታ አጋጥሞት በነበረው ህመም መጠነኛ የሳንባ ቀዶ ህክምና አድርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎ የህክምና ባለሙያዎች ተጫዋቾች ላልተወሰነ ጊዜ በአውሮፕላን እንዳይጓዝ መክረውታል፡፡
በመሆኑም ዦታ እስከ ሰሜን ስፔን በመኪና ከዚያም በጀልባ እንግሊዝ ለመድረስ ጉዞውን ቢጀመርም ካሰበበት ግን አልደረሰም፡፡
ከፖርቹጋል 190 ማይል ርቀት ላይ በምትገኘው የስፔን ግዛት ዛሞራ ውስጥ በአጋጠመው የመኪና አደጋ ላይመለስ አሸለበ፡፡
እግር ኳስ ተጫዋች ከሆነው ታናሽ ወንድሙ ጋር ህይወቱ ያለፈው ዲየጎ ዦታ ቀድሞም ቢሆን ከረጅም
ጊዜ የልጅነት ጓደኛው ጋር ጋብቻውን ለመፈጸም ወደ ሀገሩ ፖርቹጋል የተመለሰው በመኪና እና በጀልባ ጉዞ ነበር፡፡
የሶስት ልጆች አባት የሆነው ዲየጎ ዦታ ለ13 አመት አብራው ከነበረችው የፍቅር ጓደኛው ሩት ካርዶስ ጋር የሰርግ ስነ ስርአቱን ባደረገ በ11ኛው ቀን በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ አልፏል፡፡
ሚያዚያ ወር ላይ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳው አጥቂ በግንቦት ደግሞ ከሀገሩ ጋር የኔሽንስ ሊግ ክብርን አሳከክቷል፡፡
በሰኔ ወር የተሞሸረው ሰው በሀምሌ ወር መሞቱ ተሰማ፡፡ ህመሙን ላለማባባስ ከአውሮፕላን ጉዞ የራቀው አዲሱ ሙሽራ የባሰው አጋጠመው፡፡
ለተከላካዮች ፈተና የሆነው ሁለ ገቡ አጥቂ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ፖርቶ፣ ዎልቭስ እና ሊቨርፑል
ተጫውቶ ያሳለፈባቸው ክለቦች ሲሆኑ በተለይ በመርሲሳይዱ ክለብ በተሰለፈባቸው 182 ጨዋታዎች 65 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
የፕሪሚየርሊግ፣ የኤፍ ኤ ዋንጫ እና የሊግ ካፕ በቀዮቹ ቤት ያሳካቸው ክብሮች ናቸው፡፡
ገና በልጅነቱ ተሰጥኦውን ያዩ ፖርቹጋል ክርስቲያኖ ሮናልዶን የሚተካ ከኮብ አገኘች ብለው የመሰከሩለት፣ ከቁመቱ በላይ በሚያስቆጥራቸው የጭንቅላት ኳሶች አድናቆትን ያገኝው አጥቂ ለክቡም ለሀገሩም ብዙ በሚሰራበት ዕድሜው መኪና ህይወቱን ነጠቀው፡፡
ከሀገራት መሪዎች ጀምሮ እንደ ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ አይነት ከዋክብት ሀዘናቸውን ሲገልጹ የሊቨርፑል የከተማ ተቀናቃኝ የሆነው የኤቨርተን ደጋፊዎችም ጭምር ሰብአዊነትን በሚያስቀድመው እግር ኳስ አንድ መሆናቸውን ያሳዩበትም ሆነ፡፡
ሊቨርፑል ዲየጎ ዦታ ይለብሰው የነበረው 20 ቁጥር መለያ ከዚህ በኋላ እንዳይለበስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የዲየጎ ዦታ እናት እና አባትም በአንድ መጥፎ አጋጣሚ ሁለት ልጆቻቸውን ያጡበትን መጥፎ ቀን ለማሳለፍ ተገደዱ፡፡
የዲየጎ ዦታ እና የወንድሙ የቀብር ስነ ስርአት ነገ በተወለደባት ፖርቶ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
EBC
