የ ‹‹ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን›› መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዜናዬነህ ግርማ በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ በተካሄደው “የ2026 ዘላቂ የልማት ግቦች (SDG) ) ተፅዕኖ ሽልማት” ላይ አለም አቀፍ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ።
ከሽልማቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ «በዚህ ታላቅ መድረክ ሽልማቱን በመቀበሌ ከፍተኛ ክብርና ደስታ ተሰምቶኛል። እውቅናው የግሌ ብቻ ሳይሆን ዛሬ፣ ከ22 ዓመታት የወጣቶች ጋር አብሮ ከመሥራት እና ከ13 ዓመታት የዋይ.ሲ.ዲ.ኤፍ ግንባታ በኋላ፣ ትሁት፣ አመስጋኝ እና ከመቼውም በላይ ቁርጠኛ ሆኜ ቆሜያለሁ። የቡድን አባላቴ ውጤት መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ።” ብለዋል።
አቶ ዜናዬነህ አክለውም “በየቀኑ ለሚያነሳሱኝ ወጣቶች ሁሉ ይህ የእናንተም ሽልማት ነው። በየቀኑ ጠዋት ለዚህ ተልዕኮ እንድነሳ የምታደርጉኝ እናንተ ናችሁ። ይህ ሽልማት አንድ ምዕራፍ ነው፣ ጉዞው ግን አልተጠናቀቀም። በአብሮነት (SDG) 2030 እና አጀንዳ 2063 ን በወጣቶች መር እርምጃ በማፋጠን እንቀጥላለን።
የጉዞአችን መጨረሻ አይደለም። ለምን እንደጀመርን የሚያስታውስ እና የበለጠ እንድንሰራ የሚያነሳሳ ጥሪ ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች እኛን ይፈልጉናል። የአፍሪካ ወጣቶች እኛን ይፈልጉናል። እና ቃሌ ይሁን—አናቆምም።” ብለዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ ከ22 ዓመታት በላይ ሕይወታቸውን ወጣቶችን በማማከር ማሳለፋቸውን በመጥቀስ፣ በድርጅታቸው በኩል በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕይወቶችን መንካታቸውን፤ ወጣቶችን በትምህርት፣ በሥራ ፈጠራ፣ በአየር ንብረት እርምጃ እና በአስተዳደር ተሳትፎ ማብቃታቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም «የአፍሪካ ወጣቶች ነገን አይጠብቁም፤ ዛሬውኑ እየገነቡት ይገኛሉ» ሲሉ ለወጣቶች ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በዚህ ውብ ጉዞ ተሳታፊ የሆኑትን በጠቅላላ አመስግነዋል። “ቡድኔ፣ ቤተሰቤ፣ አጋሮቻችን እና ከሁሉም በላይ በየቀኑ የሚያነሳሱኝ ወጣቶችን ሳላመሰግን አላልፍም። ይህ ሁሉ እንዲሆን ለፈቀደዉ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና አቀርባለሁ።” ብለዋል።
