​«የዓድዋ ድል ለእኔና ለአዘርባጃን ሕዝብ ትልቅ ትርጉም አለው››

Date:

 

‹‹የጎንደር ሕዝብ ያሳየኝ ፍቅር ልቤን ነክቶታል››

ክቡር ሩስላን ናሲቦቭ ራፋኤል

(በኢትዮጵያ የአዘርባጃን ባለሙሉ ሥልጣንና ልዩ አምባሳደር)

ውድ የግዮን መጽሔት አንባቢያን፣ በምሥራቅ አውሮፓና በምዕራብ እስያ (በደቡብ ካውካሰስ) መገናኛ ላይ የምትገኘው አዘርባጃን ሪፐብሊክ እና የታላቋ አፍሪካ የፖለቲካ መዲናና ዋና በር የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀና ስትራቴጂካዊ ደረጃ አሸጋግረዋል፡፡

ከወራት በፊት ከፍተኛ የካቢኔ አባላትን ያካተተ የአዘርባጃን መንግሥት ልዑክ፣ በቅርቡ ደግሞ የሀገሪቱ የብሔራዊ ምክር ቤት (ሚሊ መጅሊስ) አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሳሂባ ጋፋሮቫ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋር ፍሬያማና አጠቃላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ ልዑክ በመመራት ወደ አዘርባጃን በማቅናት በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ያላትን ሰፊና የካበተ ልምድ በተመለከተ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ወደ አዘርባጃን መዲና ባኩ በማቅናት በስማርት ሲቲ፣ በከተማ ውበትና በቴክኖሎጂ ትብብር ማዕቀፎች ላይ ተስፋ ሰጪ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡

በእነዚህ ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ እንቅስቃሴዎች፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ትስስሮች እንዲሁም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕቀፎች ላይ በመመስረት በኢትዮጵያ የአዘርባጃን ባለሙሉ ሥልጣንና ልዩ አምባሳደር ከሆኑት ክቡር ሩስላን ናሲቦቭ ራፋኤል ጋር የግዮን መጽሔት ጋዜጠኞች ተረፈ ወርቁ እና ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ያደረጉትን ጥልቅ፣ አጠቃላይና አስተማሪ ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ!!

ግዮን፦ ክቡር አምባሳደር፣ በመጀመሪያ በዝግጅት ክፍላችንና በአንባቢዎቻችን ስም፣ ውድ ጊዜዎን ሰውተው ለዚህ ልዩ ቃለ-መጠይቅ ፈቃደኛ በመሆንዎ የላቀ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ውይይታችንን ከሀገርዎ ልዩ ማንነት እንጀምር፡፡ አዘርባጃንን በባሕል፣ በሕዝብና በታሪክ ረገድ ልዩ የሚያደርጋት ምንድን ነው? አገርዎትን ለኢትዮጵያውያን አንባቢዎች እንዴት ያስተዋውቋታል?

አምባሳደር ናሲቦቭ፦ ጋዜጠኛ ፍቃዱ እና ጋዜጠኛ ተረፈ፣ እንዲሁም የካሜራ ባለሙያዎች ወደ ኤምባሲያችን እንኳን በደህና መጣችሁ! ከግዮን መጽሔት ጋር ይህንን ሰፊና ታሪካዊ ቃለ-መጠይቅ በማድርጌ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡

በታሪክና በጂኦፖለቲካ ረገድ አዘርባጃን በደቡብ ካውካሰስ ቀጠና፣ በምሥራቅ አውሮፓና ምዕራብ እስያ መገናኛ ላይ የምትገኝ ልዩ ሀገር ናት፡፡ ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ ባሻገር አዘርባጃን በዓለም አቀፍ ደረጃ «የእሳት ምድር» (Land of Fire) በመባል ትታወቃለች፤ ይህ ስያሜ የመጣው ከመሬቷ ስር ባለው እጅግ የበለፀገ የተፈጥሮ ጋዝ እና የነዳጅ ክምችት ምክንያት ከጥንት ጀምሮ ከመሬቷ ውስጥ እየገነፈለ ሳይጠፋ ከሚነደው የተፈጥሮ እሳት ነው (ለምሳሌ እንደ ያናር ዳግ/ Yanar Dag ድንቅ የተፈጥሮ ክስተት)፡፡

ሆኖም የአዘርባጃን ትልቁ ሀብት የሰው ኃይሏና ማኅበራዊ እሴቶቿ ናቸው፡፡ አዘርባጃን የተለያዩ ባሕሎች፣ እምነቶች፣ ቋንቋዎችና ብሔረሰቦች ለዘመናት በሰላምና በፍቅር አብረው የኖሩባት የበለፀገ የባሕል ብዝኃነት (multiculturalism) እና የመቻቻል ምሳሌ ናት፡፡ የአዘርባጃን ሕዝብ በደግነቱ፣ በአስተናጋጅነቱ፣ ለትምህርት ባለው ፍቅርና ለነጻነት ባለው ጽኑ አቋም ይታወቃል፡፡ በምሥራቅና ምዕራብ ሥልጣኔዎች መካከል እንደ ድልድይ ሆና፣ የምሥራቅን ጥልቅ መንፈሳዊነትና የቤተሰብ እሴቶች ከምዕራቡ ዓለም ዘመናዊነትና የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር በጥበብ አዋህዳ የያዘች ሀገር ናት፡፡ ይህ ደግሞ የታሪክና የባሕል ተምሳሌት ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር በጥብቅ የሚያስተሳስር ዋና ባሕሪያችን ነው፡፡

ግዮን፦ አዘርባጃን በዩኔስኮ የተመዘገቡ በርካታ የዓለም ቅርሶች ባለቤት ናት። እነዚህን ቅርሶች ለመጠበቅ የምትከተሉት ስትራቴጂ ምንድን ነው? ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ምን ልትማር ትችላለች?

አምባሳደር ናሲቦቭ፦ የባሕል ቅርሶቻችን የሀገራችንን ታሪካዊ ማንነት የሚያስረዱ ሕያው ምስክሮቻችን ናቸው፡፡ በዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ላይ ከተካተቱት መካከል በ12ኛው ክፍለ ዘመን የተገነቡት ድንቅ የሕንፃ ጥበብ ውስብስብ አካል የሆኑት የቀደመችው የባኩ ከተማ (Icherisheher) ከሽርቫንሻህ ቤተ መንግሥትና ከሜይደን ታወር ጋር፣ ከ40,000 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸው የድንጋይ ላይ ሥዕሎች የሚገኙበት የጎቡስታን ብሔራዊ ፓርክ፣ እንዲሁም የሼኪ ታሪካዊ ማዕከል ከካን ቤተ መንግሥት ጋር ይጠቀሳሉ፡፡ ከቁሳዊ ውጪ ከሆኑት ቅርሶቻችን ደግሞ የሙጋም (Mugham) ባሕላዊ ሙዚቃ፣ የአዘርባጃን የካርፔት/ምንጣፍ ሽመና ጥበብ እና ሌሎችም በርካቶች በዩኔስኮ መዝገብ ላይ ሰፍረዋል፡፡

ዘላቂ የቅርሶች እንክብካቤ እና የከተማ ልማትን በተመለከተ የተከናወኑት፦

  1. ጥብቅ ሕጋዊና ሳይንሳዊ እንክብካቤ፦ የቀደመ ይዘታቸው ሳይበላሽና ሳይደለዝ በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ታግዞ እንዲጠበቅ ከፍተኛ የመንግሥት በጀት መመደብ፤
  2. ቅርሶችን ለቱሪዝም ማዋል፦ ቅርሶች ተቆልፈው የሚቀመጡ ሀብቶች ሳይሆኑ በቱሪዝም በኩል ሀገርን የሚያስተዋውቁና ለዜጎች ገቢ የሚያስገኙ እንዲሆኑ ማድረግ፤
  3. ማኅበረሰብን መሠረት ያደረገ ጥበቃ፦ የአካባቢው ማኅበረሰብ የአባቶቹን ቅርስ የኔ ነው ብሎ እንዲንከባከብና እንዲጠብቅ የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያም በዩኔስኮ የተመዘገቡ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ፣ የቅርሶች ጥበቃ፣ የዲጂታል ካርታ ዝግጅት እና የቱሪዝም መሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ከእኛ ጋር ሰፊ ልምድ የመለዋወጥ የጋራ ፍላጎት አላት፡፡

ግዮን፦ አዲስ አበባ ከገቡና በኢትዮጵያ የአዘርባጃን አምባሳደር ሆነው ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ያገኙት ግላዊ ምልከታ ምንድን ነው? የባሕል ለውጥ አጋጥሞዎታል ወይንስ ተመሳሳይ ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴቶችን አገኙ?

አምባሳደር ናሲቦቭ፦ ይህ እጅግ ማራኪ ጥያቄ ነው! እውነቱን ለመናገር አዲስ አበባ እንደመጣሁ ይህ ነው የሚባል የባሕል ለውጥ (cultural shock) አላጋጠመኝም፤ ይልቁንም ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ የገዛ ቤቴ የመጣሁ ያህል የሞቀ ወንድማማችነት ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡

በአዘርባጃንና በኢትዮጵያ ማኅበራዊ መዋቅር መካከል አስደናቂ ተመሳስሎዎች አሉ፡፡ የሁለቱም ሀገራት ሕዝቦች ለቤተሰብ እሴቶች፣ ለአባቶች ክብር፣ ለማኅበራዊ ግንኙነቶች፣ ለአንድነትና ለሃይማኖታዊ መቻቻል እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣሉ፡፡ በአዘርባጃን እንግዳ ወደ ቤት ሲገባ የሚደረገው አቀባበል፣ የምግብና የሻይ ሥነ-ሥርዓት በኢትዮጵያ ከሚደረገው ሞቅ ያለ አስተናጋጅነትና የቡና ሥነ-ሥርዓት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ማኅበራዊ መቀራረብ የዲፕሎማሲ ሥራዬን የተሳለጠና የተቀላጠፈ አድርጎታል፤ ምክንያቱም የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች የጋራ የሆነ የባሕል እሴቶች አላቸው፡፡

ግዮን፦ ኢትዮጵያ በምግብ ባሕሏ እና በበዓላት አከባበሯ ትታወቃለች፡፡ በኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግቦች፣ በቡና ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በብሔራዊና ሃይማኖታዊ በዓላት (እንደ መስቀል፣ ጥምቀት፣ እሬቻ፣ የዓድዋ ድል በዓል ወዘተ) ላይ ያለዎት ግላዊ ልምድ ምንድን ነው?

አምባሳደር ናሲቦቭ፦ የኢትዮጵያ የምግብ ባሕል እውነትም ልዩና ጣፋጭ ነው! በእንጀራ ከተለያዩ ማባያዎች ጋር የሚቀርቡ ባሕላዊ ምግቦችን የመቅመስ ዕድል አግኝቻለሁ፤ በተለይም ዶሮ ወጥ እና ጥብስ እጅግ የምደሰትባቸው ምግቦች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የቡና ሥነ-ሥርዓትን በተመለከተ፣ ቡና ከመጠጣት ባለፈ ሰዎችን የሚያቀራርብ፣ ፍቅርና ሰላምን የሚያበስር ጥልቅ ባሕላዊና ማኅበራዊ ጥበብ ያዘለ ሕያው ክስተት በመሆኑ እጅግ አደንቀዋለሁ፡፡

በዓላትን በተመለከተ በመስቀል አደባባይ በየዓመቱ የሚከበሩትን የመስቀልና የጥምቀት በዓላትን በግንባር የመመልከት ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ የሕዝቡ አንድነት፣ ውብ ባሕላዊ አልባሳት፣ መንፈሳዊ መዝሙራትና የሕዝቡ ቅንነት እጅግ ያስደምመኛል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የእሬቻ በዓል የምስጋናና የሰላም መግለጫ መሆኑን ተገዝበቤያለሁ፣ በዓሉ በውስጡ የያዘውን ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ታሪክ እሴቶች በይበልጥ የእርስ በርስ ትውውቅንና መተሳሰርን የሚያጠናክር መሆኑን እንዳውቅ ረድቶኛል፡፡

በተለይም የዓድዋ ድል በዓል ለእኔና ለአዘርባጃን ሕዝብ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ዓድዋ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት፣ የሉአላዊነት እና የፅናት ምልክት ነው፡፡ አዘርባጃንም በቅርብ ዓመታት የራሷን ግዛት አንድነትና ሉአላዊነት ለማስከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለች ሀገር በመሆኗ፣ ለዓድዋ ድል በዓል እና ለኢትዮጵያውያን የነጻነት ፍቅር ያለን አክብሮት ጥልቅ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ ጎንደር ውስጥ ከተመለከትኳቸው ታሪካዊ ቅርሶች ባልተናነሰ ልቤን የነካው የጎንደር ሕዝብ ያሳየኝ የሞቀ፣ የእውነተኛ ወንድማማችነትና የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት ነው፡፡ ኢትዮጵያና አዘርባጃን ረጅም ጥንታዊ ታሪክና የበለጸገ የባሕልና ሃይማኖት ብዝኃነት ያላቸው ሀገራት በመሆናቸው፣ ጎንደር ላይ ያየሁት ታሪካዊ መቻቻልና የመከባበር ባሕል ከሀገሬ አዘርባጃን የብዝኃነት እሴቶች ጋር እጅጉን ይመሳሰላል፡፡

ይህ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የባሕልና የቱሪዝም ዲፕሎማሲ ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሮልኛል፡፡ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና የተፈጥሮ ውበት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ለአዘርባጃን ሕዝብ ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጎንደር ሁልጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ጥበብና ታሪክ መገለጫ ሆና ትቀጥላለች፡፡

ወደ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ያደረግሁት ጉብኝት የኢትዮጵያን ጥበብ፣ ሥልጣኔና እውነተኛ እንግዳ ተቀባይነት በአካል የተመለከትኩበት የማይረሳ አጋጣሚ ነበር፡፡ የዓለም ቅርስ የሆነውን የፋሲል ግቢ አስደናቂ ኪነ-ሕንፃ፣ ታሪካዊውን የፋሲለደስ ባሕረ-ጥምቀት እና በሥነ-ስዕል ጥበቧ የምትታወቀውን ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተክርስቲያንን ጎብኝቻለሁ፤ ከቅርሶቹ ውበት ባልተናነሰ የጎንደር ሕዝብ ያሳየኝ የሞቀ አቀባበልና ፍቅር ልቤን ነክቶታል፡፡ በከተማዋ ያየሁት ታሪካዊ አብሮነትና የመከባበር ባሕል ከሀገሬ አዘርባጃን የባሕል ብዝኃነት እሴቶች ጋር እጅጉን ይመሳሰላል፡፡

ማስታወሻ- ውድ አንባቢያን፣ (በኢትዮጵያ የአዘርባጃን ባለሙሉ ሥልጣንና ልዩ አምባሳደር) ክቡር ሩስላን ናሲቦቭ ራፋኤል ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም ቀጣዮን ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት ይዘን የምንመለስ ይኾናል፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 235 ነሐሴ  2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የመልካም አዲስ ዓመት መግለጫ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ታደሰ ብሩ (ዶ/ር)

  ግዮን መጽሔት :-   ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ እንኳን ለ2019 ዓ.ም....

‹‹የኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት ሕዝቧ ነው›› ዶ/ር ንጉሡ ለገሠ

ግዮን መጽሔት :-  አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ብቻ...

የኢትዮጵያ የአዲስ ዓመት ነፀብራቅ ...

  ግዮን መጽሔት :-   አዲስ ዓመት ሲቃረብ ስለ አዲስ...