በዓለማችን ‹‹ሀብታም›› ከሚባሉት ሀገራት አንስቶ እስከታዳጊዎቹ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እስካሉ ሀገራት ድረስ የኑሮ ውድነት፣ የሸቀጦች ዋጋ ንረትና የገንዘብ ግሽበት የብዙኃኑ ተራው ሕዝብ የእለት ተእለት ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይ በአንዳንድ ታዳጊ ሀገራት ከምግብና መጠጥ አንስቶ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ የሆኑ እንደነዳጅን የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እየናረ፣ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን ደግሞ ለአንዳንዶች ጭራሽ የማይታሰብ እየሆነ መጥቷል፡፡ የሥራ አጥነትና የግል ንግድ እንቅስቃሴዎች መዘጋት ግን የደሀዎቹ ሀገራት ብቻ ሳይሆን የአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራትም ጭምር እየተቸገሩበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሀገሮች በየጊዜው የፋይናንስ ሥርዓታቸውና የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸው ላይ ማሻሻያዎችንና ለውጦችን ሲያደርጉ ቢታይም ለጊዜው ችግሩን ከማስታገስ ያለፈ ይህ ነው የሚባል መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አልቻሉም፡፡
በርግጥ የኢኮኖሚውን አካሄድ ግራ አጋቢ የሚያደርግ ሌላም ነገር አለ፡፡ ይህም የፋይናንስ አቅሙ ያላቸውም ሆነ በቀውስ ውስጥ እንዳሉ የሚገለጹ ሀገሮች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ሲያካሂዱ ይታያል፡፡ ኢኮኖሚያቸው በችግር ውስጥ እንዳለ የሚታወቅ ሀገሮች ፕሮጀክቶቹን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከውጭ በብድርና በእርዳታ፣ ከሀገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ግብር ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ሁለቱ ምንጮች ገንዘብ ብዙም በማይገኝበት ሁኔታ ሀገራቱ እያካሄድን ነው የሚሉትን ግዙፍ ፕሮጀክት የሚሰሩት ከየት ባመጡት ገንዘብ ነው? የሚል ጥያቄ በብዙኃኑ ተራው ሕዝብ አእምሮ ይመላለሳል፡፡
በአንድ በኩል ሀገራት እጅግ ከፍተኛ በጀት እንደመደቡ፣ ምርታቸውን ለውጪ ገበያ አቅርበውም ከቀድሞው የተሻለ ገቢ እንዳገኙ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአለም የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም የዚያኑ ያህል የምርት መጠን አድጓል፣ የአመራረት መንገዶች ተሻሽለዋል፣ ቴክኖሎጂ ምርታማነት እንዲጨምር አግዟል ፣ የመጓጓዣና የግንኙነት መሰረተ-ልማት መስፋፋትም የንግድ ልውውጥን ከበፊቱ የተሻለ እንዲሆን ረድቷል፡፡ ነገር ግን የብዙ ሀገሮች ዜጎች ኑሮ ሊሻሻል፣ የሥራ አጥነትን ቁጥር ሊቀንስ አልቻለም፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የዋጋ ንረትና የገንዘብ ግሽበት መፍትሄ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
በኛም ሀገር እንዲሁ ሸቀጦች በተቀመጡበት ዋጋቸው በየእለቱ ይንራል፣ አንዴ ከተሰቀሉ አይወርዱም፡፡ ምክንያቱ ምንድነው ሲባል መልሱ በድፍኑ ‹‹ጨምሯል›› የሚል ነው፡፡ ዶላር ጨምሯል የሚለውም እንደምክንያት ከሚቀርቡት መካከል ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ለተመረቱ ሸቀጦችም ዶላርን እንደምክንያት ለማቅረብ የሚዳዳቸውም ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ብሩ ዋጋ ስላጣ ነው የሚለውም በምክንያትነት ሲጠቀስ ይደመጣል፡፡ ለመሆኑ የአንድ ሀገር ገንዘብ በዚህ ደረጃ ዋጋ የሚያጣው በምን ምክንያት ነው? ዶላርስ በደሀዎቹም ሆነ በሀብታሞቹ ሀገራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ በዚህ መጠን ተጽእኖ ማሳደር የቻለው እንዴት ነው? ይኽ በትክክል ምላሽ ማግኘት ያለበት ጥያቄ ነው ብላ ግዮን ታምናለች፡፡
እዚህ ጋር የዶላር ተጽእኖ ወደፊት እየቀነሰ እንደሚሄድ አንዳንድ ግምቶች መኖራቸውን ጠቁመን ለማለፍ እንወዳለን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ ሀገራት ከዶላር ውጪ ሌሎች የመገበያያ አማራጮችን መጠቀም ከመጀመራቸውና የመጠባበቂያ የገንዘብ ክምችታቸውንም ከብር ኖት ይልቅ በተለይም በዶላር መልክ በውጭ ሀገር ከማስቀመጥ ይልቅ በወርቅ መልክ ማስቀመጡን አስተማማኝ መንገድ አድርገው ከማየታቸው ጋር ይያያዛል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የየሀገራት ማእከላዊ ባንኮች የሚያካሂዱት የወርቅ ግዢ በከፍተኛ መጠን በማደጉም የወርቅ ዋጋ በአለምአቀፍ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ጥያቄው ግን እውን የዶላር ተጽዕኖ በዚህ መልክ ቢቀንስ እንኳን የኑሮ ውድነቱ የዜጎችን ትከሻ ማጉበጡን ይቀንሳል ወይ የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ከውጪ የማይመጡ ዳሩ ግን ሀገሩ ውስጥ የሚመረቱ ፍጆታዎች አሁን ላይ ከውጪ ከሚገቡት ምርቶችና ጥሬ ዕቃዎች ያላነሰ እያሳዩ ያሉት ንረት እማኝ ይኾናል፡፡ አሁንም ግን እንጠይቃለን፡፡ ይኽ ሁሉ የኑሮ ውድነት ምንጩ እውን ዶላር ነውን?
ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 221 ጥር 10 2017 ዓ.ም