‹‹ከፍታ በወጣትነቴ ከማንበብና መጻፍ ጋር አስተዋወቀኝ››

Date:

እሙሽ ብርሃኑ

እሙሽ ብርሃኑ ትባላለች፡፡ የ25 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ውልደቷ እና ዕድገቷ በወላይታ ሶዶ ከተማ ቢኾንም፣ አሁን ላይ ኑሮዋን ያደረገችው ግን ሀዋሳ ከተማ ውስጥ ነው። እሙሽ ለቤተሰቧ ስድስተኛ ልጅ ብትኾንም፣ እናቷን ገና በልጅነት ዘመኗ በሞት በማጣቷ በብዙ ችግር ውስጥ ለማለፍ ተገድዳለች፡፡ በቤታቸው የነበረው ድህነትም እሙሽ ትምህርት ቤት ገብታ ቀለም የመቅሰም ዕድል እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡ ይኼ ደግሞ ከተሞች ውስጥ እየኖረች ፊርማን በጣቶቿ ለመፈረም የተገደደች ምሥኪን ሳይቀር ነበር ያደረጋት፡፡

በዚህ መልክ አስቸጋሪ ሕይወትን እየመራች የኖረችው እሙሽ የ23 ዓመት ልጅ ሳለች ግን፣ እርሷም ኾነች ቤተሰቧ የሚላስ የሚቀመስ ወደማጣት ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ፣ ከባድ የሕልውና አደጋ ከፊታቸው ተደቀነ። በዚህ ጊዜ እሙሽ የነበራት ብቸኛ አማራጭ ወደ ዐረብ ሀገር ለማቅናት የሚያስችላትን ቪዛ ለማግኘት ወደ ሀዋሳ መምጣት ነበር፡፡ ሀዋሳ ላይ ቪዛው ተሳክቶላትም ለሥራ ወደ ዱባይ አቀናች። ዱባይ ደርሳም በቤት ሰራተኛነት ሥራ መሥራት ጀመረች።

እሙሽ ያጋጠማት ሥራ እጅግ አድካሚና አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ በቀን ለ20 ያህል ሰዓታት በመሥራት ታሳልፍ ነበር፡፡ ያም ኾኖ በሥራዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ደሞዝ ተከፋይ የኾነችበት የሕይወቷ ምዕራፍ ነበርና፣ የምታገኘውን ገቢ ሀገር ቤት ወዳሉት ቤተሰቦቿ በመላክ መርዳት መቻሏን ትገልጻለች። የምታገኘውን ገንዘብ በሙሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩት ቤተሰቦቿ ትልክ የነበረች ከመኾኑ አንጻር ለራሷ የቆጠበች ቤሳ ቤስቲን አልነበረም።

እሙሽ በዚህ መልክ እየሰራች የሁለት ዓመት ኮንትራት ጊዜዋ ተጠናቀቀ፡፡ እርሷም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች፡፡ ዳሩ ግን ቤተሰቧ የላከችላቸውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ አጥፍተው ነበር የጠበቋት፡፡ እናም ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደነበረችበት የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለመመለስ ተገደደች፡፡ እጅ አልሰጥም ብላ ወደ ሀዋሳ በማቅናት ኑሮን መታገልን ጀመረች፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ሌላ ሁነት ተከሰት፡፡ አግብታ ልጅ ወለደች፡፡ ኾኖም ልጇን መመገብ ስላልቻለች ሌላ ፈተና እና ችግር ላይ ወደቀች፡፡ ወደ ዱባይ ተመልሳ ሥራ ማግኘት ትችል እንደሁ ጥረት ማድረጓን ቀጠለች፡፡

ከዕለታት በአንዱ፣ ፓስፖርቷን ለማሳደስ ወደ ኢሚግሬሽን ስታመራ፣ ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉ ወጣቶችን በመመዝገብ ላይ ከሚገኙት የከፍታ ወጣቶች ፕሮጀክት አስተባባሪዎች ጋር መገናኘት የቻለችበት ዕድል ተፈጠረ።

አስተባባሪዎቹ ስለ ፕሮጀክቱ እና ስለሥልጠናው ሁሉንም በዝርዝር አስረዷት፡፡ እርሷ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የመኖር ፍላጎት ስላልነበራት ምንም ምላሽ ልትሰጣቸው አልወደደችም። ኾኖም ስለፕሮግራሙ ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ከተሰጣት በኋላ ለመመዝገብ ተስማምታ፣ የፓስፖርት ዕድሳት ሂደቷ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሥልጠናውን እንደምትወስድ ገለጸች። ከአንድ ሳምንት በኋላ በፕሮጀክቱ የማንበብና መጻፍ ተግባራዊ ፕሮግራም ውስጥ፣ ፊደላትን የመለየት እና ለመጀመሪያ ጊዜም ሥሟን መጻፍ የጀመረችበትን ሥልጠና ወሰደች፡፡ በዚህ ጊዜ የመማር ፍላጎቷ ዕለት ዕለት እያደገ ሄደ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም የሥነ ተዋዶን ጤና ጨምሮ ልዩ ልዩ የሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎች ውስጥ ተሳታፊ መኾን ቻለች።

እሙሽ ኹነቱን ወደኋላ ስታስታውስ ‹‹በተለይ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ከወሰድኩ በኋላ ተስፋ በውስጤ ተፈጠረ ፤ የተሻለ ነገንም ማሰብ ጀመርኩ›› ትላለች፡፡ የከፍታ ወጣቶች ፕሮጀክትን ከተቀላቀለች በኋላ ያለው የሕይወት መስመሯ ወደ ዱባይ የሚያቀና እንደነበር የምትናገረው እሙሽ፣ ‹‹በእነዚያ ሥልጠናዎች ውስጥ በነበርኩባቸው እያንዳንዱ ሰዓታት ግን የአመለካከት ለውጥ ይፈጠርብኝ ነበር›› ትላለች፡፡

በርግጥም ሥልጠናው ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ ነበር የፈጠረባት፡፡ ልክ ሥልጠናው እንደተጠናቀቀ ከኢትዮጵያ ውጭ ለመጓዝ ያቀደችውን እቅድ እርግፍ አድርጋ በመተው ሀገሯ ላይ በመሥራት፣ የገዛ ሕይወቷንም ኾነ የልጇን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመቀየር ወሰነች። ፓስፖርቷን የማሳደስ ሂደቷንም ሰርዛ ሥራ ፍላጋ ውስጥ ገባች። በዐጭር ጊዜ ውስጥም በቤት ሰራተኛነት ተቀጥራ መሥራት ጀመረች፡፡ ይህ ከሕይወት ክህሎት ሥልጠናው በኋላ የጀመረችው ሥራም ቀጣይ ሕይወቷን በታላቅ ተስፋ ላይ ለማራመድ የሚያስችል የመጀመሪያ እርምጃዋ ኾነ።

የወደፊት እቅዷም በሥራዋ የምታገኘውን ገንዘብ ከፍታ ባመቻቸው የገንዘብ ቁጠባ ተቋም በመቆጠብ፣ የራሷን ንግድ ለመጀመር የሚያስችላትን ብድር ማግኘት እንደሆነ ትገልጻለች። እሙሽ ‹‹ከፍታ ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል። መጻፍና ማንበብ በመቻሌ እንኾ በአደባባይ በእስኪቢርቶ ፊርማዬን ለማኖር አልቸገርም›› በማለት በሕይወቷ ለተከሰቱት ለውጦች ሁሉ የከፍታ ፕሮጀክትን በማመስገን፣ ‹‹ከፍታ እንደኔ ባለ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የለውጥ መንገድ ነው›› በማለት ሐሳቧን ትቋጫለች፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 221 ጥር 10 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የህወሓት የቃላት ጦርነት ንሯል።ይዋጉ ይሆን?

ሶስቱም ኃይላት የጦር ኃይላቸዉን እያጠናከሩ፣ አዳዲስ ተዋጊ እየመለመሉ መሆናቸዉ...

የሐማስ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር በመተባበር የተከሰሱ ሰባት ሰዎችን ገደሉ

ሰኞ እለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ ያለ ቪዲዮ እንደሚያሳየው...