የአማኑኤል ግርማ
የ24 ዓመት ወጣቱ የአማኑኤል ግርማ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ሲኾን፣ በሥነ ልቦና ሳይንስ ተመርቋል፡፡ ኾኖም አሁን ላይ በከፍታ የወጣቶች ፕሮጀክት በኩል የሕይወት ክህሎት ሥልጠና በመውሰድ ዐዲስ የለውጥ ጉዞ ጀምሯል። የአማኑኤል ስለ ሕይወት ክህሎት ሥልጠና የቀደመ አካዳሚያዊ ዳራ እና ንድፈ ሐሳባዊ እውቀት ቢኖረውም፣ ይኽንን ዕውቀት እና ክህሎት በተግባር ከመተርጎም ጀምሮ፣ የራስን እና የሌሎችን ስሜት ተረድቶ በማረቅ ረገድ ስላሉ ጽንሠ ሐሳቦች የጠራ ግንዛቤ እንዳልነበረው በሥልጠናው ሒደት ለመገንዘብ ችሏል።
በክፍታ የወጣቶች ፕሮጀክት በኩል የአማኑኤል ያገኘው የሕይወት ክህሎት ሥልጠናም ለሕይወቱ ማርሽ ቀያሪ ኾኖ ነው ያገኘው። በሥልጠና ፕሮግራሙ አማካኝነት የአማኑኤል ግልጽ እና የጠሩ ግቦቹን መለየት ስላለው አስፈላጊነት ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ጨብጧል። ከዚያ በፊት የአማኑኤል እንዲህ ያሉ ትልሞች የነበሩት ቢኾኑም፣ ትልሞቹ ግን በአንደበቱ አልያም በማስታወሻ ደብተሮቹ ላይ ከመቀመጣቸው ውጪ፣ የተብራሩና ቅርጽ የነበራቸው አልነበሩም፡፡ የከፍታ ሥልጠና ግን የተንዛዛ ሳይኾን ለአንድ ዓመት የሚኾን የአጭር ጊዜ ግቦችን ያካተተ ዕቅድ እንዴት መንደፍ እንደሚገባው ግንዛቤን ሰጠው፡፡ እነዚህን የዐጭር ጊዜ ግቦች ቅድሚያ ሰጥቶ ለእነርሱ ውጤታማነት መትጋት የረጅም ጊዜ ግቦችን በብቃት ለማሳካት አስፈላጊ መኾኑንም በሚገባ ተማረ። እናም የአማኑኤል ያቀመጠውን ዕቅድ ከግቡ ለማድረስ ሒደቱን በዕለትና በሳምንታት ዘርዝሮ መከታተል እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ መትጋት ጀመረ።
የአማኑኤል ከከፈታ ፕሮጀክት ሥልጠና ሌሎችም ጠቃሚ ትምህርቶችን ወስዷል፡፡ ከእነዚህም አንዱ እንዴት ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን መለየት የሚችልበት ብቃት ነው። ሥልጠናው አስቀድሞ ስለራሱ ‹‹በጎ›› ብሎ የያዛቸውን ግንዛቤዎች ዳግም እንዲገመግም እና ስለገዛ ባሕሪያቱም ጠለቅ ያለ መረዳት እንዲኖረው ምክንያት ኾኖታል። እንዲህ ያለው ስለራስ የሚደረግ ግምገማ፣ የአማኑኤል ጠንካራ ጎኖቹን በደንብ እንዲለይ ያስቻለው ሲኾን፣ ይኽንንም ለራሱ እና ለሚሰራበት ሙያ ማደግ በወጉ እንዲገለገልበት ጠቅሞታል፡፡ እግረመንገዱንም ማስተካከል የሚገቡትን ባሕሪያት በማስተካከል መድረስ ወደ ሚፈልገው ግብ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲገሰግስ መንገድ ጠርጎለታል።
ለማጠቃለል ያህል፣ ከፍ ብለን የጠቀስነው የከፍታ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ፕሮግራም ለአማኑኤል ትልቅ የሚባል ለውጥን አምጥቶለታል። ሥልጠናው እራሱን በትክክል ለመገምገም እና ያሉበትን ውሱንነቶችም አጥርቶ ለመረዳት ያስቻለውን ዕውቀት፣ ቴክኒክና ዘዴ አጎናጽፎታል፡፡ ከፕሮግራሙ ያገኘው አዲስ እውቀት እና ክህሎትም ለገዛ ማንነቱም ኾነ በሙያው መድረስ ለሚፈልገው ስኬት የሚኖረው ሚና ትልቅ እና አዎንታዊ እንደሚኾን ለአፍታም አይጠራጠርም፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 221 ጥር 10 2017 ዓ.ም