ከትንግርት ወደ ሥጋት የተለወጠው ርዕደ መሬት

Date:

ከጥቂት ጊዜያት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመሬት መንቀጥቀጥ ማውራት ትንግርት ነበር፡፡ ለትንግርትነቱ ዋናው ምክንያት ደግሞ የመሬት መንቀጥቀጥ በሀገራችን ተከስቶ አለማወቁና ችግሩን ከአንዳች ተፈጥሯዊ ሁነት ይልቅ ከመንፈሳዊ መዛልና ቁጣ ጋር አገናኝቶ ማየት ነበር፡፡ ችግሩን በሩቁ የምንሰማው ቢኾንም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን የመሬት መንቀጥቀጥን ከፈጣሪ ቁጣ ጋር ማገናኘት የተለመደ እሳቤ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን አደጋው በተለይም አፋር ክልል ውስጥ የሚገኘው አዋሽ ፈንታሌ ከሰሞኑ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እያስተናገደ ነው። በሥፍራው የሚሰከተው ርዕደ መሬት ንዝረት ሩቅ ቦታዎች ላይ በተለይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ አልፎም በአዲስ አበባና እስከትግራይ ድረስም መሰማቱ የሰርክ ልማዱ ኾኗል፡፡

ሳይንሱ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰትን አስመልክቶ ልዩ ልዩ ሀሳቦችን ያነሳል፡፡ ከዚህ አንጻር ሳይንሱ እንደሚለው መሬት የተዋቀረችው በሦስት ንብርብሮች ነው። የመሬት ማዕከላዊው ክፍል “ኮር” ይባላል። ይህ ማለት ውስጠኛው ክፍል ሲኾን ቀጥሎ የሚገኘው “ማንትል” ይባላል። ይህ ማለት ደግሞ ማዕከላዊው የምድር ክፍል ሲኾን ቀጣዩና የመጨረሻው ክፍል ደግሞ “ክረስት” ወይም ቅርፊተ መሬት ይባላል፡፡ ይህ በዓይናችን የምናየው የመሬት ክፍል ነው። ክረስት እና ማንትል የላይኛው አካል ቴክቶኒክ ፕሌትስ ከተባለው ድንጋይ የተሠሩ መኾናቸውን ሳይንሱ ያስረዳል። የዘርፉ ሙያተኞች “ቴክቶኒክ ፕሌትስ” የሚሉት ሁነት ዝግ ባለ መልኩ ሁሌም ይጓዛሉ። በዚህ መካከል ግጭት እና መተፋፈግ ይፈጠራል። ይህ ግጭትና መተፋፈግም የመሬት መንቀጥቀጥ ኾኖ በመከሰት በመሬት ገጽ ላይ ያሉ አካላትን መነቅነቅና ማፈራረስን ያስከትላል ማለት ነው፡፡

በዓይናችን ከምናየው መሬት በታች ያሉት ንብርብር አለቶች በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ እርስ በርስ ሲተፋፈጉ አሊያም ሲፋጩ የመሬት የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ርዕደመሬት ይከሰታል። አንዳንድ አለቶች እርስ በርስ ተፋፍገው ሊያልፉ ይችላሉ። ኾኖም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንዱ ክፍል ከሌላኛው እየራቀ ሊሄድ ይችላል። በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ ድንጋዮች ሲተፋፈጉ ርዕደ መሬት ያስከትላሉ። የመሬት መንቀጥቀጥ የባሕር ጠለል ላይ ሲከሰት ደግሞ ከፍተኛ ማዕበል ይፈጠራል። ሱናሚ የሚባለውም ይህ እንደኾነ በቅርቡ ስለጉዳዩ ቢቢሲ አማርኛ ሰፋ አድርጎ በሠራው ዘገባ አስነብቧል።

መሬት መንቀጥቀጥ ይህ ከኾነ ዘንዳ በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የመሬት ነውጦች ይመዘገባሉ። አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ የሚባሉ እና በተለየ ቴክኖሎጂ የሚለዩ ናቸው። በጣም ከፍተኛ የሚባሉት ደግሞ ከተሞችን የማፈራረስ አቅም አላቸው። በዓለማችን ብዙ ጊዜ ተደጋጋሚ ርዕደ መሬቶች የሚከሰቱበት ሥፍራ ፓሲፊክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኘው የብሳማ አካባቢ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በፓሲፊክ ውቅያኖስ አቅራቢያ የሚገኙ እንደ ጃፓን ያሉ አገራት ርዕደ መሬትን ተላምደውታል። ሁነቱም በተደጋጋሚ ይከሰታል፡፡ አደጋውን ለመቀነስም ጃፓን ውስጥ ሕንፃዎች ርዕደ መሬትን እንዲቋቋሙ ተደርገው ይገነባሉ። በአገሪቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት አብዛኞቹ መዋቅሮች ይናጣሉ እንጂ የመፍረስ እድላቸው ዝቅተኛ ነው። ወደሀገራችን ስንመጣም ችግሩ በተደጋጋሚ የሚከሰት ኾኗል፡፡ ግዮን መጽሔትም በዋናነት ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ እየተከሰቱ ያሉ የመሬት መንቀጥቀጦችን እንደሚከተለው በየእለቱ ከተሰጡ አስተያየቶች ጋር አያይዘን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም

በአፋር ክልል በሬክተር ስኬል 4.5 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ ንዝረት አዲስ አበባ ድረስ የተሰማ ሲኾን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂዮ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ተማራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር አታላይ አየለ በወቅቱ የመሬት መንቀጥቀጡ ትንሽ ከበድ ያለና በሬክተር ስኬል 4.5  የተመዘገበ መኾኑን ለኢቢሲ ሳይበር ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጂኦፊዚክስ እና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ እንደገለጹት፤ አዋሽ ፈንታሌ አከባቢ የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ በመሬት ውስጥ አልፎ በአዲስ አበበ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች መሰማቱን ተናግረዋል፡፡  ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ በፈንታሌ ተራራ ላይ በድጋሜ በሬክተር ስኬል 4.9 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ገልጸው ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ግን የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩንም ጠቁመዋል።

ጥቅምት 01 ቀን 2017 ዓ.ም

በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ የፈለቀውን ፍል ውኃ ጥናት ሳይደረግበት ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀም ተጠይቋል፡፡ በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በዱለቻ ወረዳ ሳጋንቶ ቀበሌ አዲስ የፈለቀውን ፍል ውኃ ጥናት ሳይደረግበት ኅብረተሰቡ እንዳይጠቀም የሰመራ ዩኒቨርሲቲ አሳስቧል። የሰመራ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ምድር ትምሕርት ቤት ዲን ጌታቸው ገ/ፃድቃን በክልሉ በቅርቡ በተከሰተው እና ንዝረቱ እስከ አዲስ አበባ ከተማ ድረስ በተሰማው ርዕደ መሬት ሳቢያ በአካባቢው ከተፈጠረ የመሬት ስንጥቅ ውስጥ ፍል ውኃ መፍለቅ መጀመሩን ገልጸው ይህንን ፍል ውኃ ጥናት ሳይደረግበት ሰዎችም ኾኑ እንስሳት እንዳይጠቀሙት አስገንዝበዋል።  

ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ቀደም ሲል ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝርት ቀጥሎ ዳግም መከሰቱን ዶክተር ኤሊያስ ሊዌ ለኢቢሲ ተናገሩ። በጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጠዋት 1:37 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ ላይ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት አዲስ አበባ ድረስ መሰማቱንም ተናግረዋል። የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ባለፈው በተከሰተበት አዋሽ ፈንታሊ አካባቢ ሲኾን በሬክተር ስኬል 4.6 አካባቢ እነደኾነም ዶክተር ኤሊያስ አረጋግጠዋል። አክለውም ባለፈው በሬክተር ስኬል 4.9 በተመዘገበው ርዕደ መሬት የተሰነጠቀው መሬት 1.5 ሜትር ስፋት ያለው ስለመኾኑም ገልጸዋል። በአካባቢው የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴው እንዳልቆመ የተናገሩት ዶክተር ኤሊያስ ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ እንዳልሆነም ተናግረዋል። ለመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት የኾነው ቅልጥ አለት መሬት ውስጥ መምጣቱ መኾኑ የተናገሩት ዶክተር ኤሊያስ ይሄው እንቅስቃሴ ወደላይ አለመወጣቱንም ጠቁመዋል።

ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ለሦሥተኛ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ተሰምቷል፡፡ በአዲስ አበባ ባለፈው ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ቀጥሎ አሁንም ዳግም መከሰቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶክተር ኤሊያስ ሌዊ አረጋግጠዋል። ምሽት 5፡11 ደቂቃ ላይ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት አዲስ አበባ ድረስ መሰማቱንም ተናግረዋል። የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ባለፈው በተከሰተበት አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ሲኾን በሬክተር ስኬል 4.6 አካባቢ እነደኾነም ዶክተር ኤሊያስ ሌዊ ተናግረዋል። “በስምጥ ሸለቆ ውስጥ  ወደ መሬት ለመውጣት ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ቅልጥ አለት አሁን ረገብ  ብሎ ወደ ታች መውረድ ጀምሯል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

በአፋር ክልል አዋሽ ከሌሊቱ 8:16 እና 8:51 ደቂቃ ላይ ከፍተኛ ንዝረት ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። በአዲስ አበባም ሰሚት፣ አያት እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር፣ አልዩአምባ በ9:25 ላይ በሌሎች ቦታዎችም ንዝረቱ መሰማቱ ተገልጿል። በዚህ ዕለት ብቻ በአዋሽ ከተማ አምስት ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል።

ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ሳቡሬ ቀበሌ ጎምዲሊ በተባለ ሥፍራ እስከ 4 ነጥብ 7 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የተለያየ ደረጃ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ሠመራ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡ የመሬት መንቀጥቀጡ ከማለዳው 11 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 9 ሠዓት 21 ላይ ቢከሰትም ጉዳት አለመድረሱን በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ምድር ጥናት መምህር ኖራ የኒሞኖ ለፋና ተናግረዋል፡፡ በተለያየ ሰዓት ከተከሰተው የመሬት መንቀጥ ቀን 9 ሠዓት 21 ላይ የተከሰተው ከፍ ያለ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የአካባቢዎች ነዋሪዎች በበኩላቸው የተከሰተው ቀደም ሲል ከነበሩት ከፍተኛ መንቀጥቀጥ ነበረው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑንም አስታውቋል፡፡

ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አካባቢ ትናንት ምሽት የተለያየ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በድጋሚ መከሰቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ ሕዋ ሳይንስና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት አስታውቋል። በዩኒቨርሲቲው የሶሲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አታላይ አየለ (ፕ/ር) እንዳሉት፥ በአዋሽ ፋንታሌ ወረዳና አካባቢው የተለያየ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። ከሌሊቱ 6:13 ላይም የዕለቱ ከፍተኛው በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 6 የኾነ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ተናግረዋል። የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረትም አዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ድረስ መሰማቱን ገልጸዋል። በአካባቢው የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ መኾኑን ጠቁመው ይሁን እንጂ መጠኑ አነስተኛ ስለኾነ ስጋት እንደማይኾን አስረድተዋል። በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምድር ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ጌታቸው ገብረጻዲቅ በበኩላቸውአዋሽ ፈንታሌ የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በአካባቢው ካለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ ጋር የተያያዘ መኾኑን ጠቅሰዋል። ለአካባቢው ነዋሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄ ላይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

ታሕሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

አመሻሽ 12 ሰዓት ከ26 ላይ በፈንታሌ አካባቢ በሬክተር ስኬል 5 የኾነ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታወቋል፡፤ የመሬት መንቀጥቀጡ በተደጋጋሚ እየተስተዋለ መኾኑንም በዩኒቨርሲቲው የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም የሴስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ሣይንስ መምህርና ተመራማሪ አታላይ አየለ (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡ ባለፈው በዚሁ አካባቢ በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ 3 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አውስተው ካለፈው አንጻር የዛሬው ጠንከር ማለቱን አስረድተዋል፡፡

ታሕሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

በአዋሽ አካባቢ ዛሬ ምሽት በሬክተር ስኬል 5.0 የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል፡፡ በዚህ ዕለት ብቻ ሰባት የመሬት መንቀጥቀጦች ተመዝግበዋል፡፡ በአፋር ክልል አዋሽ አካባቢ በሰሞኑ ከደረሱት የመሬት መንቀጥቀጥ ክሰተቶች በመጠኑ ከፍተኛ የኾነ ርዕደ መሬት በዚህ ዕለት ምሽት መከሰቱን የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል አስታወቋል። በአካባቢው ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ10 ላይ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በሬክተር ስኬል 5.0 የደረሰ እንደኾነ የማዕከሉ መረጃ አመልክቷል። በሬክተር ስኬል የመለኪያ መሳሪያ ከ2.5 እስከ 5.4 መጠን ያላቸው የመሬት መንቀጥቀጦች አነስተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ እንኾኑ በዘርፉ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ይገልጻሉ።

ታሕሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ልክ 4:18 ላይ ከአዋሽ 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሬክተር ስኬል 4.8 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አመላክቷል። ይህ 4.8 ኾኖ የተለካው የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፈው ለሊት ከተመዘገበው ከፍተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ተመሳሳይ ነው። ታሕሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ከጥዋት አንስቶ የተለያየ መጠን ያላቸው በርካታ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች ተመዝግበው የነበረ ሲኾን ከፍተኛው 4.8 ነበር። በዚህ ዕለትም አዋሽ እና አካባቢው ላይ 4.3 እና ከዚያ በላይ የተመዘገቡ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች ነበሩ።

ታሕሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

ከ4:41- 4:46 ደቂቃ በአዲስ አበባ አራት ኪሎ፣ ሰንጋተራ፣ ሚኒልክ ሆስፒታል፣ ላምበረት.. እና በሌሎች አካባቢዎች ከሰሞኑ ከባድ የተባለ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ተሰምቷል፡፡ በዚህ ዕለት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ መነሻው አዋሽ አካባቢ ሲኾን የመሬት መንቀጥቀጡ ካለፉት ቀናት ከፍተኛ ሲኾን 5.2 በሬክተር ስኬል ተመዝግቧል። በ24 ሰዓታት ውስጥም ከ13 በላይ የመሬት መንቀጥቀጦች ተመዝግበዋል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጦቹ ሌሊት ላይ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ሲኾን ንዝረታቸው በሬትከተር ስኬል ከ4.4 እስከ 4.8 አልፎም 5.2 ማግኒትዩት መካከል መመዝገባቸው ተጠቁሟል፡፡

ታሕሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ በሬክተር ስኬል 5 ኾኖ የተመዘገበ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ተሰምቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ በሬክተር ስኬል 5 ኾኖ የተመዘገበ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት የተሰማ ሲኾን በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በአዲስ አበባ ተደጋጋሚ የመሬት ንዝረት መከሰቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ አረጋግጠዋል።  በአካባቢው ያለው የቅልጥ ዓለት ድንጋይ (ማግማ) እንቅስቃሴ አሁንም በመቀጠሉ የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እንዲከሰት ማስቻሉን ዶ/ር ኤሊያስ ጨምረው ገልጸዋል።

ታሕሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

በአዋሽ ፈንታሌ ምሽት 2:01 ሰዓት ላይ ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ የተሰማ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል። በዩኒቨርሲቲው የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የሴስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አታላይ አየለ (ፕ/ር) እንዳሉት በአካባቢው የተለያየ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ነው፡፡ ምሽት 2:01 ሰዓት ላይ በፈንታሌ ዙሪያ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 3 እንዲሁም ቀን 11:27 ሰዓት ላይ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 2 የኾነ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ተናግረዋል። በዚህ ዕለት በተከታታይ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት ሰሞኑን ከታዩት ሁሉ ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል። በአካባቢው በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ በመኾኑ ነዋሪዎች ላይ ችግር እንዳያስከትል የቅርብ ክትትል እንዲደረግም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ታሕሣሥ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

በአዋሽ ኤፍራታና ግድም ወረዳ ምሽት 5:05 ላይ ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ የተሰማ በሬክተር ስኬል 5 ኾኖ የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂ ሰርቬይ መረጃ አመልክቷል፡፡  ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በአዋሽ አካባቢ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ሲኾን፤ ምሽቱን በሬክተር ስኬል 5 ኾኖ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች የተሰማ ነበር። ትናንት ሌሊት 9 ሰዓት አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በኢትዮጵያ እስካሁን ከፍ ያለ እንደነበር የተነገረ ሲኾን የመሬት መንቀጥቀጡ በሬክተር ስኬል 5.8 ኾኖ ተመዘግቧል፡፡

ጥር 01 ቀን 2017 ዓ.ም

በአንድ ሰዓት ውስጥ ሶስት የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል፡፡ አዳሩን ከተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛው በሬክተር ስኬል 5.2 የተመዘገበ ሲኾን የተከሰተው ከለሊቱ 9:19 ከአዋሽ በስተሰሜን በ30ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው፡፡ በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ ከፍተኛ የተባለ ንዝረት ተሰምቷል። ለሊት የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥም ለሊት 8:42 በአፋር ገርባ ከአዋሽ ሰሜናዊ ምዕራብ በ12ኪ.ሜ ርቀት በሬክተር ስኬል 4.60 የኾነ፣ ለሊት 8:58 አማራ ክልል ብጨንቀኝ በሬክተር ስኬል 4.50 የኾነ፣ ለሊት 9:19 ከአዋሽ ባስተሰሜን በ30ኪ.ሜ ርቀት የምሽቱ ከፍተኛ የኾነ የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 5.20 የኾነ፣ ለሊት 10:50 ከመተሐራ በደቡባዊ ምስራቅ በ25ኪ.ሜ ርቀት በሬክተር ስኬል 4.30 የኾነ፣ ጠዋት 12:22 ከመተሐራ በደቡብ አቅጣጫ በ28ኪ.ሜ ርቀት በሬክተር ስኬል 4.40 የኾኑ የመሬት መንቀጥቀጦች ተመዝግበዋል።

ጥር 04 ቀን 2017 ዓ.ም

ከምሽቱ 4:49 በመተሐራ አቅራቢያ በሬክተር ስኬል 5.1 የተመዘበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። ንዝረቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች ተሰምቷል።

ጥር 05 ቀን 2017 ዓ.ም

ምሽት 5:24 ሲል በሬክተር ስኬል 4.8 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ከአዋሽ 17 ኪ/ሜ ርቀት ላይ መከሰቱን የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አሳውቋል። የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ አዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች ተሰምቷል።

ጥር 06 ቀን 2017 ዓ.ም

በአፋር ክልል የመሬት መንቀጥቀጥ የሚስተዋልባቸዉ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ በዉሃ ሊዋጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለ በአፋር ክልል የዞን 3 ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዶ አሊ አቡበከር  ገልፀዋል፡፡ በአካባቢው ጥናት እያደረጉ ያሉት ከአዲስአበባ እና ከሰመራ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ የጂኦሎጂ ተመራማሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ያለባቸው ቦታዎች  በውሃ ሊዋጡ ስለሚችሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ቦታውን መልቀቅ እንዳለባቸው ማስታውቃቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ መሰል የተፈጥሮ ክስተት በሚስተዋልበት ወቅት ተገማች የሚደረጉ ሁኔታዎች የሚነሱ  ሲሆን ይህም  አካባቢዎቹ በዉሃ ሊዋጡ ይችላሉ የሚል ሳይንሳዊ ግምገማዎች መቀመጡን የጥናት ቡድኑ አባል ኖራ የኒምኦ አስታወቀዋል። የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አብዶ አሊ ዜጎችን ከስፍራው የማንሳት እና ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወር ስራ እየተስራ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም ከአዋሺ ፈንታሌ ወረዳ አራት ቀበሌዎች እና ከዱላቻ ወረዳ ደሞ ሁለት ቀበሌ ነዋሪዎችን እንዲሁም የከሰም ስኳር ፋብሪካን ሠራተኞች ከስጋት ቀጠና በማንሳት ወደ ተሻለ ቦታ ማስፈር ተችሏል ብለዋል፡፡

በጥቅሉ ግን የመሬት መንቀጥቀጥ በሚያጋጥም ጊዜ መደረግ የሚገባቸዉ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንዳሉ የዘርፉ ሙያተኞች ተከታዮቹን ምክሮች ለግሰዋል፡፡

  • ከቤት ውጭ ከኾኑ ከዛፎች፣ ከሕንፃዎች፣ ከኤሌትሪክ ምሶሶዎች እና ሌሎች ወድቀው ጉዳት ሊያደርሱ ከሚችሉ ነገሮች መራቅ እና ገላጣ ሜዳ አካባቢ መቆየት።
  • በቤት ውስጥ ከኾኑ በበር መቃኖች፣ በኮርነሮች እና ኮሪደሮች ተጠግቶ ማሳለፍ። ከእሳት ምድጃዎች፣ ከተሰቀሉ ፍሬሞች እና የግድግዳ ጌጦች፣ ከመጽሐፍ መደርደሪያዎች እንዲሁም ከመስኮት አካባቢ መራቅ። የጋዝ ምድጃዎችን በተቻለ ፍጥነት ማጥፋት ካልኾነም ከአካባቢው መራቅ።
  • በትልልቅ ሕንጻዎች ውስጥ ከኾኑ ከሕንጻዎቹ ለመውጣት አለመሞከር፣ አሳንሰር (ሊፍት) በፍፁም አለመጠቀም። ከደረጃዎች አካባቢ መራቅ።
  • መኪና እያሽከረከሩ ከኾኑ የኤሌክትሪክ መተላለፊያ ምሶሶዎችን፣ ዛፎችና ሽቦዎች አካባቢ አለመቆም፣ የኤሌትሪክ መስመር ምሶሶዎች እና ሽቦዎች ተሽርካሪው ላይ ከወደቁ ከመኪናው ለመውጣት አለመሞከር፣ በተቻለ ፍጥነት ገላጣ ወደኾነ አካባቢ መኪናን ማቆም ከጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል መኾናቸውን ከእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 221 ጥር 10 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

“ሕገ መንግሥቱ መገንጠልን ይፈቅዳል ፤ ሕዝቡ ደግሞ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ዋጋ ይከፍላል”

አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል(የ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› መጽሐፍ ደራሲ) ግዮን መጽሔት :-...

ባለሙያ ባልሆኑ ግለሰቦች የሚሰራጭ የተዛባ መረጃ በታካሚዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነዉ

የሳይካትሪስት የሙያ ፈቃድና ሥልጠና የሌላቸው ግለሰቦች በተለያዩ መገናኛ...

የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና የ1.2 ቢሊዮን ዩሮ ስምምነት ሊፈራረሙ ነው

በአውሮፓ ህብረት እና በኢትዮጵያ መካከል በሚካሄደው የንግድ ፎረም መክፈቻ...

የአዳዲስ እና የሁለተኛ ዙር መራጮች አቅምና ሚና

ግዮን መጽሔት :- በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የአዳዲስ (ለመጀመሪያ...