የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መቀመጫውን ካናዳ ካደረገው “ፊውቸር ፊት ኢንተርናሽናል” ጋር በክህሎት ልማትና በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዙሪያ በቅንጅት መሥራት የሚያስችለንን ስምምነት በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር መፈራረሙን መግለጹ ይታወሳል።
ስምምነቱ ዜጎችን በክህሎት አብቅቶ ለዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ለማቅረብ የሚረዳና በካናዳ መንግሥት ሙሉ ዕውቅና ያለው በመሆኑ፣ ወደ ካናዳ የሚደረገውን የዜጎች ስምሪት በሕጋዊ መንገድ ለመምራት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ተብሎለት ነበር።
ይህን ተከትሎ በርካታ አሳሳች ማስታወቂያዎች ሲሰራጩ ቆይተዋል። በተለያየ ጊዜም ከሚኒስቴሩ ጨምሮ ወደ ካናዳ የሥራ ስምሪት አለመጀመሩን ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህን አስመልክቶም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት “ካናዳ፤ ምዝገባም ሆነ ስምሪት አልተጀመረም!” ሲል ገልጿል።
ከዚህ ቀደም የተፈጸመው ስምምነትም በዋነኛነት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን ገልጿል።
ስምምነቱም በዋነኛነት በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ብቻ ያተኩራል፦
• ከካናዳ ኮሌጆች ጋር በመተባበር ተማሪዎችን በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ በሚፈለጉ ክህሎቶች ማሰልጠን፤
• ብቁ የሆኑ ተማሪዎች በካናዳ በሚገኙ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት የነፃ ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማመቻቸት።
ከዚህ ስምምነት ውጪ ሚኒስትሩ “ሚኒስቴሩ ወደ ካናዳ ህጋዊ የሥራ ስምሪት ጀምሯል” በማለት የተሳሳተ መረጃ ከሚሰጡ፤ “ወደ ካናዳ እንልክዎታለን” በማለት ከፍተኛ ገንዘብ ከሚጠይቁና “ከሚኒስቴሩ ህጋዊ ውክልና ተሰጥቶናል” ከሚሉ አጭበርባሪዎች ዜጎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል።
አያይዞም፥ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ስምምነት ወደ ተፈራረመችባቸው ሀገራት በህጋዊ መንገድ ዜጎችን በመሰማራት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
ሀገራቱም ፦
🇸🇦 ሳውዲ አረቢያ
🇦🇪 የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ
🇯🇴 ጆርዳን
🇶🇦 ኳታር
🇱🇧 ሊባኖስ
🇰🇼 ኪዌት ናቸው።
ሚኒስቴሩ አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ በ9138 በነፃ የስልክ መስመር ወይም info@mols.gov.et እና በአቅራቢ በሚገኝ የህግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቋል።
