ጤና ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰራ አንድ ወጥ የሆነ የጤና መታወቂያ ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ይህ አዲስ አሰራር ከብሔራዊ መታወቂያ ጋር በሚናበብ መንገድ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ የጤና ስርዓቱን በማሻሻልና የማኅበረሰብ የጤና መረጃ አሰባሰብን ለማቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ፤ “ይህ ሥራ የዲጂታል የጤና ስርዓትን ለማስፋፋት እየተደረገ ካለው ሰፊ ጥረት ጋር የተያያዘ ነው” ብለዋል፡፡
ሚንስትሯ በማብራሪያቸው፤ አዲሱ ወጥ የጤና መታወቂያ ስርዓት ተግባራዊ ሲደረግ የመረጃ ክፍተትን ያሻሽላል አገልግሎት አሰጣጥን ያቀላጥፋል ብለዋል፡፡
የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም መረጃዎችን በዘመናዊ መንገድ እንዲሰበስቡ የሚያግዝ አሰራር እየተዘረጋ እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል።
ይህ አሠራር በተለይም በማኅበረሰብ ደረጃ የሚገኙ የጤና መረጃዎችን በፍጥነት በመሰብሰብ የሚፈጠረውን የመረጃ ክፍተት የሚያቀል ይሆናል።
ይህንን አዲስ አሠራር በመጠቀም እስካሁን ድረስ 29 ሚሊየን የሚሆኑ በከተማ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን መመዝገብ መቻሉን ወይዘሮ ሳህረላ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የዲጂታል የጤና ስርዓትን ለማስፋት በሚሰራው ሥራ ውስጥ ባንኮች እና ሌሎችም አገልግሎቱን ማቅረብ የሚችሉ ተቋማት ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገልጿል።
