ዋስትና አልባ የብድር አገልግሎት በጥንቃቄ ካልተመራ ለቀውስ ሊዳርግ ይችላል

Date:

የፋይናንስ ተቋማት በመተግበርያዎች አማካኝነት ያለ ማስያዣ እየሰጡ የሚገኙት ፈጣን ብድር አነስተኛ እና ጀማሪ ተቋማትን በመደገፍ የኢኮኖሚ እድገትን የማፋጠን አበርክቶ ቢኖረውም፤ “በጥንቃቄ ካልተመራ ኢኮኖሚውን ለቀውስ የማጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው” ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

እንደ ባለሙያዎቹ ማብራሪያ ያለ ማስያዣ እስከ አንድ ሚልዮን ብር ድረስ እየተሰጠ ያለው ብድር በዕውቀት እና በጥንቃቄ ካልተመራ፤ በተበላሸ ብድር ምክንያት ኪሳራ የሚያስመዘግቡ ባንኮች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያውና ፖለቲከኛው አቶ ጌትነት ወርቁ በዋስትና አልባ ብድር ምክንያት የፋይናንስ ተቋማት ሊገቡበት የሚችሉትን አደጋ ሲያስረዱ፤ “ያለ ተመጣጣኝ ማስያዣ የበዛ መጠን ያለው ብድር የሚያቀርብ የፋይናንስ ተቋም የተበላሸ ብድር ሲኖር ገንዘቡን መልሶ የሚያገኝበት መንገድ አይኖረውም” ብለዋል። 

“ተበዳሪው ሲከስር ተቋሙ አብሮ ይከስራል፤ ተቋማቱ ከከሰሩ ደግሞ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ለመደጎም ይገደዳል” ሲሉም ገልጸዋል።

አሜሪካ በባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመን አጋጥሟት የነበረውን የፋይናንስ ቀውስ ያስታወሱት አቶ ጌትነት፤ “ኢትዮጵያ ባንኮችን የመደጎም አቅም ላይ ስላልደረሰች በጥንቃቄ መጓዙ አማራጭ የለውም” ብለዋል።

ሌላው የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው ዋስትና አልባ የብድር አቅርቦት በጎ ገጽታ እንዳለው ጠቅሰዋል።

“በፋይናንስ ተቋማት በቅርቡ የተጀመረው ዋስትና አልባ የብድር አቅርቦት ከዚህ ቀደም የንግድ ሐሳብ እያላቸው በዋስትና እጦት ምክንያት ወደ ተግባር መግባት ያልቻሉ ዜጎችን ወደ ሥራ በማስገባት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል” የሚሉት ባለሙያው፤ የዚህ ዓይነቱ የብድር ሥርዓት ዋነኛው ጥቅሙ የፋይናንስ ተደራሽነትን ማስፋፋት እንደሆነ አስረድተዋል።

ዋስትና አልባ ብድር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ቢሆንም፤ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በዚህም “ተቋማቱ አደጋን ለመቀነስ የክትትልና ግምገማ ሥርዓት ማጠናከር ይኖርባቸዋል” ያሉ ሲሆን፤ ብድር የተሰጣቸው ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እና የተበዳሪዎች የገንዘብ አጠቃቀም በየጊዜውና በጥብቅ ሁኔታ መከታተልና መገምገም አለባቸው የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል። ይህ ካልሆነ ግን የብድር የመመለስ አደጋ ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

“አገልግሎቱ ሁለት ገጽታ አለው” ያሉት ባለሙያዎቹ፤ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ይህንን አዲስ አሠራር በጥንቃቄና በስፋት ተግባራዊ በማድረግ እንደሚገባቸው መክረዋል።

አሐዱ ራዲዮ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አበባው ደሳለው (ዶ/ር) ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲና ተሳትፎ ራሳቸውን አገለሉ

የቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)...

ኢትዮጵያ በወጣቶች ኦሊምፒክ አራተኛዋን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች

በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር እየተካሄደ ባለው አራተኛው የወጣቶች ኦሊምፒክ...

በወራቤ ሆስፒታል የተመረቀው የኦክስጅን ፋብሪካ በሰዓት 60 ኪዩቢክ ሜትር የማምረት አቅም እንዳለው ተገለጸ

በወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተመረቀው የኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ በሰዓት...