አሜሪካ በሶማሊያ የሚገኘውን የአይ ኤስ አይ ኤስ የፋይናንስ ኦፕሬሽን ክንፍ በተመለከተ መረጃ ለሚሰጥ ሰው የ10 ሚሊየን ዶላር ሽልማት እንደምትጥ አስታወቀች።
የአሸባሪው አይ ኤስ አይ ኤስ በአፍሪካ ዋነኛ መቀመጫ ናት በተባለችው ሶማሊያ የሚገኘው የፋይናንስ ክንፍን አስመልክቶ መረጃን ለሚሰጣት ግለሰብም ሆነ ተቋም ሽልማት እንደምትሰጥ ነው አሜሪካ ያስታወቀችው።
የፋይናንስ መረጃዎችን የሚሰጡ ሰዎች ከገንዘብ ሽልማቱ በተጨማሪ ደህንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ እንደሚዘዋወሩም ተገልጿል።
አሜሪካ ቡድኑ በማጭበርበር ፣ በመዝረፍ እንደዚሁም ሰዎችን በማገት ገንዘብ ይሰበስባል ያለች ሲሆን በተጨማሪ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ህገ ወጥ የአሳ ማስገር ተግባራት ትርፍ እያገኘ ነው ብላለች።
አይ ኤስ አይ ኤስ ሶማሊያ በ2015 በአብዱልቃድር ሙሚን አመራር ስር የተመሰረተ ሲሆን ይኸው ግለሰብ በ2025 ወደ አይ ኤስ አይ ኤስ አለም አቀፍ አመራርነት አድጓል ተብሏል።
አሜሪካ በቅርቡ በሶማሊያ ያለው አል ካራር የተባለ ቢሮ የቡድኑ የፋይናንስ ማዕከል ሆኖ እየሰራ መሆኑን መግለጿ ሲታወስ በክሪፕቶከረንሲ መልክ ገንዘቡ እንደሚዘዋወርም ገልፃ ነበር።
አይ ኤስ አይ ኤስ ለአፍሪካ ቀንድ አሁንም ስጋት ሲሆን በቅርቡ ኢትዮጵያ በፑንትላንድ ሰልጥነዋል የተባሉ 82 አባላቱን መያዟ መዘገቡ ይታወሳል ሲል ሀገሬ ዘግቧል።