በግጭት ምክንያት ከቤታቸው የተፈናቀሉትን ዜጎች አስመልክቶ የተደረገ ፈጣን ዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ 71 በመቶ የሚሆኑት ተፈናቃዮች በቂ ምግብ እንደሌላቸው፣ እንዲሁም 80 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ምግብን እንደ ዋና እና አስቸኳይ ፍላጎታቸው አድርገው መለየታቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ሞያሌ በነበረው ግጭት ሳቢያ ከቤታቸው ተፈናቅለው ወደ ኬንያዋ ሞያሌ የገቡ 50 ሺህ ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) እና አጋር አካላት ጥሪ አቅርበዋል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ ከግጭት ሸሽተው ድንበር አቋርጠው ወደ ኬንያ ከገቡት መካከል የተወሰኑትን በማካተት በኬንያ ባለሥልጣናት፣ በተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካይነት ፈጣን የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል።
በተጨማሪም በዳሰሳው ከቤተሰቦች መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት በቂ የመጠጥ ውኃ እንደሌላቸው የተናገሩ ሲሆን፣ ከሦስት አራተኛ በላይ የሚሆኑት ደግሞ እጅ መታጠቢያ ስፍራዎች እንደሌላቸው ጥናቱ አሳይቷል።
የጤና አገልግሎት እጥረትን በተመለከተ ደግሞ ከፍተኛ የመድኃኒት ዋጋ እና የህክምና አገልግሎት እጥረት በዋናነት በመጥቀስ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦች የጤና አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ገልጸዋል።
አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ከዘመዶቻቸው እና ከአስተናጋጁ ማለትም ከኬንያ ማህበረሰብ ጋር እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በምግብ፣ በውኃ እና በመጠለያ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። ሌሎች ደግሞ በትምህርት ቤቶችና ጊዜያዊ ስፍራዎች እንዲሁም ከቤት ውጭ ሜዳ ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
ከተፈናቀሉት ውስጥ 96 በመቶ የሚሆኑት ከኦሮሚያ እና ከሶማሌ ክልሎች የሸሹ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ዜጎች መንደራቸው በሙሉ ለፍልሰት እንደተዳረገ ተናግረዋል። ከደረሱት ስደተኞች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸው በከፋ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን ህጻናት ጤና እና ደህንነት አስመልክቶ ስጋት ደቅኗል ሲል አስታውቋል።
የአይ.ኦ.ኤም የኬንያ የሥራ ኃላፊና ሌሎች አካላት የተፈናቃዮችን እና የአስተናጋጅ ማህበረሰቦችን አስቸኳይ ፍላጎቶች ለማሟላት አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ አበክረው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ሦስት ሚሊዮን ዶላር መበጀቱ ይታወሳል።
