ግዮን መጽሔት :- ቱሪዝም ትኩረት ያገኘ ኢንዱስትሪ ሆኗል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሁሉን ትቶ ሁሉን የሰጠው እስኪባል አጀንዳ የሆነ ኢንዱስትሪ ነው፡፡
ያሳለፍነው አንድ ዓመት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ጉልህ ክስተቶችን አስተናግዷል፡፡ አሁንም የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ችግር እንደ ጣና፣ ስሜን ተራሮች፣ አክሱም እና የትግራይ መስህቦች ጉብኝት ላይ መጥፎ ጥላውን እንዳጠላ ነው፡፡ እንደ ጎንደር እና ላሊበላ ያሉም ቅርሶች በውጪ ጎብኚ ቁጥር ወቅታዊው ሁኔታ ጥላ አጥልቶባቸዋል፡፡
በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ የሚቆጠሩ ተግባራት የተከናወኑበት ዓመት ነው፡፡ አዲስ አበባ ለማመን በሚከብድ መጠን ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉባኤዎችን አስተናግዳለች፡፡ ማይስ ቱሪዝም የኢትዮጵያ መፃኢ ዕጣ ፈንታ መሆኑ በሚገባ የተረጋገጠበት ዓመት ነበር፡፡ አዲስ አበባ ባሳለፍነው ዓመት ከ200 በላይ ጉባኤዎችንም አስተናግዳለች፡፡
በመሠረተ ልማት ረገድም አዳዲስ መዳረሻዎች ተጠናቀው ተመርቀዋል፡፡ በወሎ ከደሴ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሎጎ በተባለው ሐይቅ ላይ የተሰራው ሪዞርት የተመረቀው ባሳለፍነው ዓመት የካቲት ወር ነበር፡፡ በ13 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በገበታ ለትውልድ ፕሮግራም የተሰራ ሲሆን ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምግብ ቤቶችን፣ የመዋኛ ገንዳዎችን፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶችን እና የሄሊኮፕተር ማረፊያን ጨምሮ በተለያዩ የፍራፍሬ ዞኖች እና ለዓይን የሚማርኩ አረንጓዴ ስፍራዎች ያሉት ነው፡፡
በተመሳሳይ በወሩ መጋቢት 2018 የተመረቀው ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ሌላኛው በ’ገበታ ለትውልድ’ ውጥን የተሰራ ሎጂ ነው፡፡ ሎጁ 78,000 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ተፈጥሯዊ የፍልውሃ መዋኛ፣ ሁለት ግዙፍ ሰው ሰራሽ ሐይቆች እና 3.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእግር ጉዞ (ሀይኪንግ) መንገድ አካቷል፡፡ የግል መዋኛ ገንዳ ያላቸው ሁለት ፕሬዝዳንታዊ ቪላዎች፣ አስራ ሁለት እርስ በእርስ የተያያዙ የመኝታ ክፍሎች እና አስራ ስድስት ባለ አንድ መኝታ ቤቶችን ጨምሮ ዘመናዊ የምግብ አዳራሾች፣ የእንግዳ መቀበያ ህንፃ፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የቢሮ ክፍሎች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ እና ሁለት ሄሊኮፕተሮችን በአንድ ጊዜ ማሳረፍ የሚችል ስፍራ (ሄሊፓድ) መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለታል፡፡
ይህ የገበታ መርሐ ግብር የግሉ ዘርፍም ተሳትፎበታል፡፡ በባህር ዳር የተገነባው እና በሚያዚያ ወር የተመረቀው ፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት ሌላው የቱሪዝም መሰረተ ልማት ነው፡፡ በደቡባዊ የጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ ያረፈው ይህ ሪዞርት፣ ከጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ጋር በመቀናጀት የጣናን ተፋሰስ የቱሪዝም መዳረሻነት ከፍ የሚያደርግ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ሲሆን በቤአኢካ ንግድና ኢንቨስትመንት ስር በሚገኘው ሮዳ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ አማካኝነት በ4.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ነው፡፡
በሰኔ ወር የተመረቀው የአርባ ምንጩ ገበታ ለትውልድ ሌላው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ የስብሰባ አዳራሽ እና በሐይቅ ላይ የተገነባ ልዩ ተንሳፋፊ ሬስቶራንትን በውስጡ ያካተተው ይህ ፕሮጀክት ግዙፍ የቱሪዝም አቅም ነው፡፡
በመሰረተ ልማት ረገድ በግልም ዘርፍ ብዙ መነቃቃቶች የተፈጠሩበት ዓመት መሆኑን እረዳለሁ፡፡ እንደ አካባቢያዊ አስተዳደሮች በከምባታ፣ ጎፋ፣ ጋሞ፣ ካፋ፣ ወላይታ ሶዶ አካባቢዎች እየተሰሩ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ስራዎች በአካባቢው አስተዳደር ተነሳሽነት የተጀመሩ ናቸው። የከተማ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችም በቀጥታ ለቱሪዝም መሰረተ ልማት ሌላ ትልቅ ዕድል ይዘው መጥተዋል፡፡
የአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት መስፋፋትም በአዳዲስ ቀጠናዎች ስለ ቱሪዝም ተስፋ እንድናደርግ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ሐምሌ ወር የተመረቀው የደብረ ማርቆሱ አየር ማረፊያ በቀን ሦስት በሳምንት 21 በረራዎችን ያስተናግዳል፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ቀጠና ሚዛን አማን የተገነባው ኤርፖርትም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ኤርፖርቱ ለኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ሌላ አማራጭ መሆን የቻለ ነው፡፡
በሌላ በኩል የዓለምን ትኩረት ለመሳብ የተሰሩ ሥራዎችም ነበሩ፡፡ እንደ አይሻው ስፒድ (IShowSpeed) እና እንግሊዛዊው ዲላን ፔጅ (Dylan Page) የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የኢትዮጵያን መልካም ገፅታና ቱሪዝም ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቱሪስት የሚልኩ ዓለም አቀፍ አስጎብኚ ድርጅቶችን የመሳቡና ኢትዮጵያን የማሳየቱ ጉዳይ ውስንነቶች አሉበት፡፡
በዓመቱ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ልቆ የታየባቸው ቀጠናዎች አሉ፡፡ ይህንን በተመለከተ መንግሥት በ2019 ዓመት ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ጉብኝት በማድረግ ከ79 ቢሊዮን ብር በላይ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም የገንዘብ ዝውውር መፍጠር መቻሉን ይገልፃል፡፡
በእኔ ዕይታ ላቅ ባለ ሁኔታ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ከተመለከትኩባቸው መዳረሻዎች ወንጪ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በየሳምንቱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወደ ወንጪ ይጓዛሉ፡፡ ይህ ጉዞ ለብዙ የጉዞ አዘጋጆችም ሆነ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
እንደ ወንጪ ሁሉ የበሰቃው ቤኑና እና የአፋሩ ድሆ ሎጆችም በተመሳሳይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቀልብ የሳቡበት ዓመት ነው፡፡ በብሔራዊ ፓርኮች ረገድ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርኮች እና ነጭ ሳር በስፋት የተጎበኙ ናቸው፡፡
የተፈጥሮ ቱሪዝም ዘርፍን የሚደግፈው በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ፈንድ (Global Environment Facility – GEF) ስምንተኛው የፋይናንስ ዑደት የተባለው የGEF-8 ፕሮጀክትም ይፋ የሆነው በዚህ ዓመት ነው። የሶፍ ዑመር እና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች የቀጠሉበት ዓመት ሲሆን በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክም ከ KFW በተገኘ ድጋፍ የሶስት መቶ ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ግንባታ ተበስሯል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት የፀጥታው ችግር በተለይም እንደ ደቡብ ኦሞ ባሉ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ ችግሮች ተባብሰዋል፡፡ አስጎብኚዎች በመንገድ ላይ ተገድለዋል፡፡ የሰሜኑ ኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር እንደ አክሱም እና ላሊበላ ባሉ ከተሞች የሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ጎድቷል፡፡
አዲሱ ዓመት በመጣ ቁጥር የሰላም የጤና የብልፅግና ዓመት ይሁንልን ብለን እንመራረቃለን፡፡ አዲሱን ዓመት የሰላም ያድርግልን እንጂ በቱሪዝም አዲስ ነገር የምናይበት እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 236 መስከረም 2019 ዓ.ም
