የአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በአሁን ወቅት ባጋጠመው የአዉፕላን እጥረት ምክንያት የዓመታዊ የተሳፋሪዎች ቁጥር ዕድገቱ ከታቀደው በታች መሆኑን አስታወቀ።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በቅርቡ ከብሎምበርግ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ እንዳስረዱት፣ አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከ12 እስከ 15 በመቶ የሚደርስ የሁለት አሃዝ ዕድገት እያስመዘገበ ነው።
አቶ መስፍን ይህንን አስመልክቶ ሲናገሩ፦ “አሁን ባለው ሁኔታ በአውሮፕላን እጥረት ምክንያት ዕድገታችን ከ15 በመቶ በላይ መሆን አልቻለም። ይህ እጥረት ባይኖር ኖሮ ከ15 በመቶ በበለጠ ፍጥነት እናድግ ነበር” ብለዋል።
የአቅርቦት መስተጓጎሉ በዋነኝነት የሚታየው ሰፊ አካል ያላቸዉ አውሮፕላኖች ላይ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ሊቀጥል እንደሚችል አመላክተዋል።
ይሁን እንጂ፣ አየር መንገዱ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከዋና ዋና አምራቾች የሆኑትን ቦይንግ እና ኤርባስ ጨምሮ በርካታ ሰፊ አካል አውሮፕላኖችን በብዛት ለመቀበል መታቀዱን ገልጸዋል።
ይህ አዲስ ግዥም የአጭር ጊዜ ዕድገት መገደብን በመቀልበስ የረጅም ጊዜ ዕድገት ዕቅዱን ለማሳካት ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።
CapitalNews
