የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ጋር እንዲወዳደሩ ቢፈለግም ሊሳካላቸው አልቻለም

Date:

የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ጋር እንዲወዳደሩ ቢፈለግም በፖሊሲ እና በሌሎች ጉዳዮች ሊሳካላቸው እንዳልተቻለ ገለጹ፤ አዲሱ የዳግም ምዝገባ መስፈርትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመስፋፋት ይልቅ ለመዘጋት እየዳረጋቸው መሆኑ ተሰማ።

ይህ የተባለው የግል ከፍተኛ ትምህርት እና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ማህበር በዛሬው ዕለት ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ጋር የግሉ ዘርፍ በትምህርት ላይ ያለባቸውን ፈተናዎች እና አስተዋጽኦን በተመለከተ በተወያየበት ወቅት ነው።

ዳግም ምዝገባን በተመለከተ በርካታ የግል ተቋማት መስፈርቱን ማሟላት ባለመቻለው ስድስት እና አስራ ሁለት ወር ተሰጥቷቸው እንደነበር ተነስቷል። በዚህም ጊዜ ያሟሉ፣ በአንጻሩ መስፈርቱ ያገዳቸው መኖራቸው ተመላክቷል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው አንዳንድ መስፈርቶችን በተመለከተ “የመንግስት ተቋማት መስፈርቱን አያሟሉም ከተባለ ታዲያ የግል ተቋማት እንዴት ሊያሟሉ ይችላሉ” ሲሉ በጥያቄ አዘል መልኩ ያለውን ችግር አመልክተዋል። አክለውም፤ ማህበሩ ለህገወጥ የትምህርት ተቋማት ጥብቅና እንደማይቆም አንስተው፤ በዚህ ጉዳይም ከመንግስት ጎን በመቆም ህግና ሥርዓትን ተከትሎ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ መንግስት የሚያወጣቸው መስፈርቶች እና ህግጋት የግሉን ዘርፍ ያገናዘበ እና በአስቻይ ሁኔታዎች ላይ የተመረኮዘ መሆን እንዳለበት አጽዕኖት ተሰጥቷል።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሞላ ጸጋይ (ዶ/ር) እንደገለጹት ከሆነ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየመጡ ያሉ አዳዲስ አሰራሮች በግሉ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ናቸው፡፡

እንዲሁም በመርሐ ግብሩ ላይ ከመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ጋር እንዲወዳደር እንደሚፈለግ በማንሳት፣ ነገር ግን ህጉ እኩል ካልሆነ እንዴት ተወዳዳሪ መሆን ይቻላል የሚል አስተያየት ከተሳታፊዎች ቀርቧል።

ትምህርት ሚኒስቴርን በመወከል በመድረኩ የተገኙት ኢባ ሚጀና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግሉን ዘርፍ ለማሳደግ የፖሊሲ እና የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች እንዲሁም ጥናት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
አክለውም የግል ተቋማት ቀጣይነት እንዲኖራቸው ልዩ የሚያደርጋቸውን ጉዳይ መያዝ እንዳለባቸው አንስተዋል። በተጨማሪም በሀገሪቱ ያሉ ተቋማት ተመሳሳይ የትምህርት ዓይነት እንደሚሰጡ አክለዋል።

ይህን ጉዳይ ሲገልፁም በሀገሪቱ 47 የመንግስት ዩኒቨርሲቲ መኖሩን ጠቅሰው፣ በሚሰጡት የትምህርት ክፍል ዓይነት ግን “አንድ ዩኒቨርስቲ 47 ካምፓስ” አለን እንደማለት ነው ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም ዩኒቨርስቲዎች የተለያዩ ፕሮግራሞችን ማለትም ልዩ የሚያደርጋቸውን መስጠት መጀመር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ዶክተር ሞላ አክለውም፤ አሁን ላይ ዳግም ምዝገባ ተቋማትን አደጋ ላይ ከመጣሉ በተጨማሪ የሚቀላቀላቸውም ተማሪ እየቀነሰ መሆኑኑን ጠቁመዋል። ይህም በግል ብቻ ሳይሆን በመንግስትም እንደሆን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው የሬሜድያል ፕሮግራምን በተመለከተ የግል አስተያየቴ ነው ያሉት ሞላ “ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም ስርዓት እየመሰለ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ይህም ጉዳይ መቅረት እንዳለበት እና የማለፊያ ነጥብን በመቀነስ ከዛ በኋላ ያለው ላይ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የመውጫ ፈተና ለምን በግሉ የትምህርት ተቋማት የሚያልፉት አነስተኛ እየሆነ መጣ ለሚለው ምላሽ የሰጡት የማህበሩ የቦርድ አባል የሆኑት ዶክተር ተረፈ ፈየራ፤ ሁሉም እንደ አንድ እየተፈረጀ መሆኑን አንስተው፣ ከመንግስት ዩኒቨርስቲ በላይ የሚያሳልፉ መኖራቸውን በመጠቆም ይህ ግን ለምን ሆነ የሚለው ጥልቅ የሆነ ዳሰሳ እና ጥናት ያስፈልጋል ብለዋል። በተለያየ መልኩ መፈተሽ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

Addis Maled

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በሆርሙዝ አቅራቢያ ሁለት መርከቦች ጥቃት ከተፈጸመባቸው በኋላ መስመጣቸው ተነገረ

የባሕር ትራንስፖርት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ባለፉት አስር ቀናት በወሽመጡ ላይ...

የዳንጎቴ ነዳጅ ማጣሪያ የአክሲዮን ሽያጭ

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የዳንጎቴ የነዳጅ ማጣሪያ ኩባንያ አክሲዮኖች...

‹‹ሕገመንግሥታዊ ተቃርኖዎች››   ያራቆተው የተቃርኖ ገመና

በደረጀ ይመር   ማስፈንጠሪያ ግዮን መጽሔት :-    የአብርሆት ዘመን ፍሬ የሆነው...

የኢትዮጵያ እና የቻይና አየር መንገዶች የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ቻይና ሳውዘርን አየር መንገድ በቻይና...