የ“ግድቡ የኔ ነው“ ባለቤት

Date:

የዘመናት ቁጭት የነበረው ዓባይ ለወግ ማዕረግ በቅቷል፡፡ እህህታ ሳይሆን የእሰዬው ዘመኑ መጥቷል፡፡

እነሆ ሊሞሸር በሰርጉ ዋዜማ ላይ ተገኝቷል፡፡ ለግድቡ ዕውን መሆን በየዘመናቱ የህይወትም ጭምር ዋጋ የከፈሉለት እልፍ ናቸው፡፡

በዓባይ ድግስ ላይ የማይዘነጉ በርካታ ግለሰቦች አሉ፡፡

ከነዚህ መካከል አንዱ መምህር ነበሩ፤ በአስተማሪነት ትውልድን ሲቀርጹ ኖረዋል፡፡

ለአምስት ዓመታት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስቴርንም መርተዋል፡፡ በየሄዱበት የስራ ዘርፍ ውጤታማ ሰው ናቸው፡፡

ለዓመታት በተወጡት የሥራ ኃላፊነት ምክንያትም የዘጠነኛው የበጎ ሰው ተሸላሚ ነበሩ፡፡ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፡፡

ሰውዬው “ግድቡ የኔ ነው” የሚለው መልዕክት ባለቤት ናቸው፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፤ አንድ የውጭ አገር ጋዜጠኛ ግድቡ ሲጠናቀቅ አስተዳዳሪው ማነው በሚል ለተጠየቁት ምላሻቸው “ግድቡ የኔ ነው“ የሚል ነበር፡፡

ይሄ ቃልም በህዝቡ ተጋብቶ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አገልግሏል፡፡ ታግሎ ማታገያ፣ ሞግቶ መጣያ ሆኖም ጠቅሟል።

በሚንስትርነት ዘመናቸው በሕዳሴው ግድብ ምክንያት ኢትዮጵያ ቅርቃር ውስጥ ገብታ ነበር። ሽፋኑ ድርድር ይሰኝ እንጂ ጉዳዩ የሚመለከታቸም የማይመለከታቸውም ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ ዘምተው የነበረው፡፡

ሚንስትሩም ስምምነት ተደረሰም አልተደረሰም ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ መሙላቷን አታቆምም የሚል የፀና አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡

እሳቸው አንደበተ ርቱዕ ናቸው፡፡ እለቱ በኢትዮጵያ የጊዜ ቀመር በ02/11/13 ዓ.ም ነበር፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ቀርበው ንግግር አደረጉ፡፡ ይህ ንግግራቸውም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ አስቀራቸው፡፡

‹‹እየገነባን ያለነው ግድብ እንጂ ኒውክሌር ማብላያ አይደለም›› በሚለው ቆፍጣና ንግግራቸው ይታወቃሉ፡፡

ሙሉ የዚህ ሀሳብ ንግግራቸውም “እዚህ ምክር ቤት ተገኝቶ ያስረዳ የመጀመርያው የውሀ ሚኒስትር ሳልሆን አልቀርም፣ ጉዳዩ ወደዚህ ምክር ቤት መምጣቱ በራሱ አግባብ አይደለም፤ ምክንያቱም እየገነባን ያለነው የውሀ ግድብ እንጂ የኒውክሊየር ማብላያ አይደለም”።

ንግግራቸው “የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ላብ፣ ደም እና እንባ እየተገነባ ያለ ነው ይህም ልዩ ያደርገዋል” የሚል ነበር፡፡

“በየሀገሩ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ሲንከራተቱ ተሰድደው የሚኖሩ፣ የባህር ሲሳይ የሆኑ፣ የሚሞቱ የኢትዮጵያ ልጆች በሀገራቸው ኮርተው መኖር ያምራቸዋል፤ ደግሞም ይገባቸዋል።” ብለው ነበር፡፡

በዓለም አቀፉ ውሃ አስተዳደር ተቋም በርካታ የምርምር ስራዎችን አከናውነዋል፤ በዘርፉ ላይ የሚያጠነጥን መፅሃፍም አላቸው፡፡

የዓለም አቀፉ ውሃ አስተዳደር ተቋም የናይል ተፋሰስ እና ምሥራቅ አፍሪካ ክልላዊ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ለሰባት ዓመታት መርተዋል፡፡

ኒው ዮርክ በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥ የማኅበራዊ ጉዳዮች ክፍል የኢኮኖሚና ዘላቂ ልማት ላይ ክልላዊ አማካሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡

በአሜሪካ የተድላ ኑሯቸውን ትተው ሀገራቸው ያደረገችላቸውን ጥሪ ተቀብለው በዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱት ኢንጅነር ስለሺ በቀለን ኢትዮጵያ ታመሰግናቸዋለች፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ደቡብ ሱዳን የነዳጅ ቅድመ-ክፍያ ውሎችን እንዳትፈጽም አገደ

የለንደን ፍርድ ቤት ደቡብ ሱዳን ከአሁን በኋላ አዳዲስ የነዳጅ...

” ከ140 በላይ ጠጠር አምራች ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል ” – ማህበሩ

" ካላቸው ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ። ግን መሬቱ መቼ እንደተወሰደባቸው...

ትራምፕ “በኢራን ላይ ሊፈጸም ታቅዶ የነበረውን ጥቃት አንፈጽምም” አሉ

ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ቁልፍ የአሜሪካ አጋር ሀገራት መሪዎች...

በነዳጅ ጭማሪ በኬንያ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የአራት ሰዎች ሕይወት አለፈ

በኬንያ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በጸጥታ...