የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የ2017 ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ነገ እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም የደርጋል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዘላቂ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት በ2014 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት ኢንዱስትሪውን ማሳደግና ተወዳዳሪ ማድረግ፣ ለአምራች ኢንዱትሪው ምቹ የቢዝነስ ከባቢያዊ ሁኔታን መፍጠር እንዲሁም በሀገር ውስጥ ትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመፍጠር መዋቅራዊ ሽግግሩ እውን እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ ንቅናቄው መጀመሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አበባ ታመነ ገልጸዋል፡፡
የንቅናቄውን 4ኛ አመትን አስመልክቶ ከተዘጋጁ መርሃ ግብሮች መካከል የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ አበባ ዓላማውም አምራች ኢንዱስትሪዎች በስፖርቱ ዘርፍ መዋለ ንዋያቸውን አፍስሰው አስፈላጊ ምርቶችን በማምረት ድጋፍ እንዲያደጉ እና በሀገር ውስጥ አምራቾች የተመረቱ የስፖርት አልባሳትን ለማስተዋወቅ እንዲሁም አስፈላጊውን የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫው መነሻና መዳረሻውን መስቀል አደባባይ የሚያደርግ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የ300,000.00 ፣የ200,000.00 ፣ የ100,000.00 የብር ሽልማቶች መዘጋጀታቸውን እንዲሁም በሁለቱም ጾታዎች በክለብ ደረጃ ተወዳድረው ከ 1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች ሽልማት መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
