(ፍልስፍናን ከነነፃነቷ የኖራት፣ በልዩ ትወና የሰበካት አይረሴ ምሁር!)
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የነበረውን የጴሌ ዳሮታን (ዶ/ር) ህልፈት የሰማ ከቀድሞ ተማሪዎቹ የሆነ ‹‹አሳፍ ኃይሉ›› በማኅበራዊ ትስስር ገጹ፤ ስለ ጴሌ (ዶ/ር) ካሰፈረው ረዘም ያለ የታሪክ ማስታወሻ በጥቂቱ ቀንጨብ አድርጌ ወደ እኔው ጥቂት ትዝታ ለማለፍ ወደድኹ፤
የዕውቁን የፍልስፍና መምህራችንን የዶ/ር ጴሌ ዳሮታን ህልፈት ሰማሁ። ከልብ አዝኜያለሁ።
በእርግጥ ፔሌ ቀጥታ የእኔ አስተማሪ ሆኖ ባያውቅም፣ ዝናውን በመስማት ጉዱን ለማየት ከጓደኞቼ ጋር ከአንድም ሁለት ቀን በእርሱ ሌክቸር ክፍለጊዜ ገብቼ ሎጂክን እንደ መደሰቻ ሽቶ ተርከፍክፌ ነው የወጣሁት ብል ማጋነን አይደለም!
ጴሌ በጣም ቀልደኛ ሰው ነበረ። ስሙን በእንግሊዝኛ “Pelle” ብሎ ይፅፍና፣ ዕድሜ ለእንግሊዝኛ “ጴ” የሚል ፊደል ስለሌለው ስሜን ከጴሌ ወደ ፔሌ ቀየረልኝ — በማለት ያሳቀንን አልረሳውም!!
የፍልስፍና መምህሩን ጴሌ ዳሮታ (ዶ/ር) በጨርፍታ በእኔው ትውስታ!!
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ፍልስፍናን ነፍስ ከዘሩበት ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፤ በ1990ዎቹ አዲስ አበባ ተማሪ በነበርንበት ጊዜ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መከፈቱ ስለነበር ከሌላ የትምህርት ክፍል/ዲፓርትመንት እያስፈቀድን ጴሌ የሚያስተምርበት ክፍል እንማር ነበር፡፡
አንድ ወቅት ላይ ስለ እውነት/What is Reality በሚል አርእስት የግሪክ ፈላስፋዎችና ጥልቅ አሳቢዎች/Philosophers and Great Thinkers የተናገሩት/የተጻፉትን ሐሳብ እያስተማረን ሳለ፤ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚያደርገው በሌክቸሩ መካከል አንድ ጥያቄ ለእኛ ለተማሪዎች እንዲህ ሲል አነሳ፤
‹‹እውነት ለእናንተ ምንድን ነው፤ ማነው?››
ተማሪዎች እርስ በርስ እየተያየን ዝምታን አሰፈንን… ‹‹በሉ እንጂ አያዞአችሁ ባትመልሱት አያሰቀላችሁም እኮ!›› ሲል ለማደፋፋር ሞከረ፡፡ ከጥቂት አፍታ በኋላ ከፊት ተቀምጦ የነበረ ተማሪ ፍርሃትና ሥጋት በቀላቀለ ድምፀት፤
‹‹ለእኔ እውነት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!›› ሲል መለሰ፡፡
ጴሌ፡- መላጣውን አሸት አሸት እያደረገ ‹‹እረ ባክህ… ተው እንጂ… ይሄኔ በእርሱ ዘመን ኖረህ ቢሆን ኖሮ ሲወገርና ሲሰቀል አንዱ ድንጋይ አቀባይ አንተ ትሆን ነበር?!›› ሲለው? ክፍሉ በሣቅ አውካካ…፡፡
ከዚህ በፍርድ ወንበር ፊት ከተቀመጠው ከጲላጦስ፤ ‹‹እውነት ምንድ ነው?›› ጥያቄ ጋር በተያያዘ ጴሌ አንድ በገሃዱ ዓለም የሆነ ይሁን ወይም እርሱ የፈጠረው ታሪክ ይሁን ለጊዜው ትዝ ባይለኝም አንድ ታሪክ እንዲህ ሲል አወጋን፤
በናዚ ዘመን አይሁዶች በያሉበት እየታደኑ በመርዝ ጋዝ ሲያልቁ በነበረበት ክፉ ጊዜ የነበሩ አንዲት አይሁዳዊት እናት እና ልጀ ተደብቀው ይኖሩ ነበር፡፡ ይህቺ አይሁዳዊት እናት ለብቸኛው ልጇ እንዲህ እያለች ትነግረው/ታስተምረው ነበር፤
‹‹ልጄ እውነትን ውደድ፤ ሁሌም እውነት ተናገር!››
ታዲያ አንድ ወቅት ላይ የናዚ አሳሽ ወታደሮች በጥቆማ ወደ ቤታቸው ይመጣሉ፤ ወታደሮቹ በሩን ሲያንኳኩ ልጅ በሩን ይከፍታል፤ ልጁን በጥያቄ ያፋጥጡታል፤ ‹‹እዚህ ቤት ውስጥ አንተ ብቻ ነህ የምትኖረው?››
ልጅ ይመልሳል… ‹‹አይ እናቴም አለች ግን እናቴ በታችኛው ምሥጢራዊ ክፍል ውስጥ ነው ያለችው፤›› በማለት የናዚ ወታደሮችን እናቱ ወዳለችበት ይመራቸዋል፡፡
ወታደሮቹ እናቱን እና ልጁን ይዘዋቸው ሄዱ፤ የእናቲቱና የልጁ ዕጣ ፈንታ እንደ ወገኖቻቸው ሁሉ በመርዝ ጋዝ ጭስ ተቃጥሎ፣ ታፍኖና ተልብልቦ መሞት ሆነ…
ጴሌ፡- ታሪኩን ተርኮ ከጨረሰልን በኋላ የተለመደውን ጥያቄው አስከተለ፤
‹‹ለመሆኑ ለዚህ የግፍ ሞት ተጠያቂው ማነው… እናት ወይስ ልጅ ወይስ የናዚ ወታደሮች?! ከመመለሳችሁ በፊት ጥቂት አስቡ ዝምምም ብላችሁ እንዳመጣላችሁ እንዳትመልሱ… ጎበዝ ‹‹F›› ለማግኘትም እኮ ትንሽ ማሰብ፤ ማሰላሰል ይጠይቃል…፤›› ዳግመኛ ክፍሉ በሳቅ ማእበል ተናወጠ…
ጴሌ እንዲህ ዓይነት የፍልስፍና መምህር ነበር… ነፍሱ በጥበብ ፍቅር የነደደች…!!
ጴሌ ዳሮታ (ዶ/ር) ነፍስህ በሰላም ትረፍ!!
