በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ በታጣቂዎች ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸው ተሰማ። ጉዳቱ ትናንት ማለዳ ሦስት ሰዓት ገደማ ላይ የተፈጸመው በአኝዋ ወረዳ ከዲማ ወደ ጎክ ይጓዝ በነበረ በአንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ነው።
የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃት አድራሾቹ ከደቡብ ሱዳን ድንበር አልፈው የገቡ የሙርሌ ታጣቂዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። የዲማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኡጁሉ ኡማን በበኩላቸው ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ ከጥቃት አድራሹቹ አንዱ በመገደሉ የሙርሌ ታጣቂዎች መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደተቻለ ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ አውቶቡሱን በማስቆም በሁለት አቅጣጫ ጥቃት ማድረሳቸውን እና በወቅቱ ከተሳፋሪዎቹ አንዱ የፖሊስ ባልደረባ በመሆኑ ጥቃቱን መከላከሉንም አስረድተዋል። በዚህም ጥቃት አሽከርካሪውን ጨምሮ አምስቱ መገደላቸው ሌሎች ስድስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጧል። አሁን ማምሻውን በደረሰን መረጃ መሠረትም ቆስለው ወደ ሀኪም ቤት ከተወሰዱት አንደኛው ማረፋቸውን ከአሶሳ ነዳሳ ደሳለኝ ገልጿል።
