“የእግዚአብሔርን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል”
ከዓምደ ብርሃን ገ/ፃድቅ
“እግዚአብሔር አለ፤ ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታታም ይሁኑ፤ በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናትን ይሁኑ፤ እግዚአብሔር ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን ትንሹ ብርሃን በሌሊት እንዲሠለጥን ክዋክብትንም ደግሞ አደረገ፤” (ዘፍጥ 1፥14-19) በማለት ጸሐፊው ሙሴ እንደተናገረው እግዚአብሐር አምላክ ለፍጥረታት ሁሉ ሕይወታዊ እንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ የሆኑት በተለይም የሰው ልጅ ሠርቶ የሚያርፍባቸው፣ አርፎም የሚሠራባቸውን ዕለታትንና ዓመታትን በመለየት ኑሮውን በሥርዓትና በመርሐ ግብር የሚመራባቸውን እነዚህ ሦስት ዐበይት ነገሮችን በመፍጠሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ሁኔታ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ብዙ ዕለታትና ዓመታት እየተመላለሱ ለ5 ሺህ 500 ዘመናት ያህል ዐውደ ዓመታት ቢፈራረቁም ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኩነኔ፣ ከመባል በስተቀር ዓመተ እግዚአብሔር ዓመተ ምህረት ተብሎ የተሰየመና የተለየ ዓመት አልነበረም፡፡
ከዚህ በኋላ ያለውን ዘመን ግን ቸርነቱ የበዛ አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳንና የሰጠውን ተስፋ ለመፈጸም ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሰው ሆኖ ወንጌልን በየአገሩ ተመላልሶ በማስተማሩ ለታሠሩት መፈታት፣ ለዕውሮች ማየት፣ ለተጠቁት ነፃነት ስለታወጀበትና በአጠቃላይ ወንጌል ለድሆች የተሰበከበት ዘመን በመሆኑ ዓመተ ፍዳው በዓመተ ምሕረት ተተካ፤ ዘመኑ ዘመነ ወንጌል ዓመቱም ዓመተ ምሕረት ተባለ፤ ስለዚህ ነው ነቢዩ ኢሳይያስ በርዕሱ እንደተገለጸው “የእግዚአብሔርን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል፤” ሲል የተናገረው፡፡
ማዕዶት፤ መስከረም 1985ዓ.ም
መስከረም ሲጠባ የክረምቱ ቀናት አይፈጸሙም
ልሣኑ በዛብህ
ዘመን ያልፋል ዘመን ይተካል እንጂ አዲስ ዘመን በየዓመቱ እየተፈጠረ አይመጣም፤ ያው ያለፈው ዘመን ተመልሶ ሲመጣ አዲስ ስለሚመስለን አዲስ ዘመን እያልን እንሰይመዋለን፡፡ ዘመን ለሰው ልጆች መዘጋጃ፣ መልካም ሥራ መሥሪያ፣ መክበሪያ ነው እንጂ ዘመን ሰዎችን አይሠራቸውም፤ አይፈጥራቸውም፤ አያዘጋጃቸውም፤ አያከብራቸውም፣ አያመሰግናቸውም፡፡
መስከረም ሲጠባ የክረምቱ ቀናት አይፈጸሙም፤ ገና 25 ቀኖች ይቀራሉ፤ ግን ዘመኑ አዲስ ይባላል፤ በደመና ተሸፍኖ የቆየው ሰማይ ደመናው እየተገለጠ፣ ኀብረ ፀሐይ እየሞቀ፣ አበቦች እየፈኩ፣ ነጐድጓድና መባርቅት ድምጻቸውን እየቀነሱ፣ የደፈረሱ ውሀዎች እየጠሩ፣ ጭቃዎች ጠፈፍ እያሉ እየደረቁ ይታያሉና ክረምቱ አልቆ መፀው የተተካ ይመስላል፡፡ የተራቡትም ፍጡራን እሸት እየበሉ ስለሚጠግቡ ከሐምሌና ከነሐሴ ወራት ይልቅ መስከረም የጥጋብ ዋዜማ ነው ሊባል ይቻላል፡፡ ከውሃ ሙላት የተነሣ ተለያይተው የከረሙት ቤተሰቦች እየተገናኙ ለመነጋገርና ለመመካከር የሚችሉትም ወርኃ መስከረም ወርኃ ተንከተም… የዘመን ድልድይ ሊባል የሚገባው ወር ነው፡፡
የአበቦች ገጽታ
ኤፍሬም በየነ
ዓለማችን ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ዕለታት በወራት እየተቀመሩ ዓመታት በተለዋወጡ ቁጥር ለተተኪው ዘመን በምድራችን ላይ ልዩ ገጸ በረከት ሆነው የሚቀርቡት አበቦች ናቸው፡፡ እንደ ሀገራችን የወራት አቆጣጠር ለወሮች ሁሉ መጀመሪያ የሆነው መስከረም ሲሆን ይህ ወር ከባተ በኋላ ሠርቀ ወሩ እየተገባደደ ሲሄድ ከሰኔ ወር ጀምሮ በጠለ ዝናም እየለመለመች የቆየችው ምድር አበቦችን ትጎናጸፋለች፡፡ በውበቷ የፍጡራንን ዐይን ትማርካለች፤ መልካሙ የአበቦች ሽታም ሕሊናን ይስባል፡፡
አበቦች ለምድራችን ልዩ ገጽና ሀብት እንደሆኑ ነቢዩ ኢሳይያስ በእግዚአብሔር መንፈስ ተቃኝቶ “ምድረ በዳና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፡፡ በረሃውም ሐሴት ያደርጋል፤ እንደ ጽጌረዳም ያብባል፤ እጅግ ያብባል፤ በደስታና በዝማሬ ሐሴትን ያደርጋል” በማለት ጽፏል፡፡ ቀደም ሲል በነበሩት ጠበብት አስተሳሰብ ያማሩና የተወደዱ አበቦች ውበት ባለፈው የብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ሰዎች ቁንጅና ተመስሎበት እናገኛለን፡፡
ይህም “እኔ የሳሮን ጽጌረዳ የቈላም አበባ ነኝ፤ በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ…” ሲል ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌ የተናገረውን ስንመለከት የአበቦች ውበት እንደሚያስደስት ሁሉ የሰዎችንም ውበት (ቁንጅና) ለመግለጽ ጠቢቡ ሰሎሞን ከሰጠው ምክር መገንዘብ እንችላለን፡፡ አበቦች ምንም እንኳ ውበታቸው ያማረና ተወዳጅ ቢሆኑም ብዙ ጊዜ አይቆዩም፡፡ ፈጥነው በፀሐይ ይደርቃሉ ወይም ደግሞ ወደ ፍሬነት ይለወጣሉ፡፡
ይህንንም ነቢዩ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ከሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት ጋር እያገናዘበ ሲናገር “አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ፤ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያፈራል፤ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ ያልፋልና…” በማለት እንደገለጸው አበቦች አምረውና ሠምረው ቢታዩም የበጋው ጊዜ እየበረታ ሲሄድ ፈጥነው እንደሚጠፉ ሁሉ የሰው ልጅ በምድራዊ ሕይወቱ ዘመን ገኖና ከብሮ ቢታይም ፈጥኖ እንደሚጠፋ ከአበቦች ጋር በማገናዘብ ይመክራል፡፡
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ስለ አዲስ ዘመን
ጳጉሜ 6 ቀን 1935 ዓ.ም ከተናገሩት የተቀነጨበ፡-
ዛሬ ከዘመን ወደ ዘመን ከሕዝባችን ጋራ ያሸጋገረንን አምላክ በምናመሰግንበት ሰዓት በዚህ ዓመት ለአገራችንና ለዓለም እግዚአብሔር የፈጸመለትን ሥራ ለሕዝባችን ስናስታውቅ ለወደፊት ለምንሠራው ሁሉ ወደ ትክክለኛው መንገድ መሪ እንዲሆነን ተስፋ እያደረግን ነው፡፡
ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር ኃይል በድል አድራጊነትዋ ከሦስት ሺህ ዓመት ጀምሮ የሥልጣኔ እርምጃዋን ስትራመድ አውሎ ነፋስ ተነሥቶ አናወጻት፡፡
ይህም አውሎ ነፋስ የጸጥታ ሥራዋን አቋረጠባት፡፡ ጉዳቱ ለዓለም በመላ እንደሚተርፍ ብታስታውቅ ለጊዜው ሰሚ በማጣቷ እጅግ አሳዝኖ ነበር፡፡ ነገር ግን አውሎ ነፋስ ጉዳት ቢያመጣ በቅጽበተ ዓይን ማለፉን ስለተረዳነው የሚያልፍበትን ሰዓት በሙሉ ተስፋ በመጠባበቅ አቆይቶን ሲያልፍ አሳየን፡፡ ነቢያት አባቶቻችን ትዕቢተኛውንና ዓመፀኛውን በአንደበታቸው ሲገርፉት የተናገሩት ነገር ደረሰ፡፡
ሰማየ ሰማያት እወጣለሁ፣ ከልዑል አምላክ ጋር እቀመጣለሁ ሲል የነበረው ተምዘግዝጎ እንጦርጦስ ወረደ፡፡ ትናንትና ለኢትዮጵያ አሳቢ ለመሆን ሲፈክር የነበረው ለራሱ የሚታሰብለት ሆነ፡፡ ነቢዩ እንዳለው “አፈር ምንጣፍህ፣ ትል መጐናጸፊያህ፤ ሆኖ መበስበስህን ተመልከት፡፡ ከወደቅህበትም ሕዝብን አላሳርፍ ብሎ የነበረው ይህ ነውን?” እያሉ እርሱን ከበው ያደንቃሉ፡፡
በዘመናት ውስጥ በባቢሎን በፅርዕ፣ በሮም፣ አውሎ ነፋስ ሆነው ዓለምን ለጥቂት ጊዜ ያናወጧት ሁሉ ምነው ታሪካችን ልብ ሳያስገዛህ ቀረ የሚሉት ሆነው ይታዩናል፡፡
ትናንትና በማይጨው ጦርነት “ከእንግዴህ ወዲህ ማባረር ነው እንጂ ጦርነት የለብንም” ሲል የነበረው ጠቅላይ የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ዛሬ በራሱ የደረሰበትን አስቀድሞ ያናገረው ሆኖ ይታያል፡፡
በዚህ አዲስ ዓመት ለእግዚአብሔር ምስጋና በምናቀርብበት ሰዓት ለሕዝባችን አንድ አንድ ነገር እንዲታሰባችሁ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
የእንግሊዝና የአሜሪካ ጦር በሚያስገርም ተዋጊነት የኢጣልያን ጦር ያላንዳች ውል በፍጹም ድል ሆኖ እጁን እንዲሰጥ ሲያደርግ በዚሀ ዘመን በሚለወጥበት ቀን ዋዜማ እንዳጋጣሚ ደርሶ ተፈጸመ፡፡
…የንጉሠ ነገሥት መንግሥታችን ሥራ የተቋቋመበት ጊዜና ሁናቴ የሚያስቸግር ቢሆን እንኳ እግዚአብሔር እንደሚረዳን ሙሉ እምነት አለን፡፡ የጨለማው ሰዓት፣ ብርሃን ሆኖ እየታየ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ በጣልነው መሠረት ደንጊያ ላይ በዚህ በአዲሱ ዘመን በዝግታ በትእግስት የሚፈጸመውን ሕንፃ እየቀጠልንበት እንሄዳለን፡፡
… አምላክ ለሰው ዘር ባደረገለት ታላቅ ሥራው ምስጋና ይግባው፡፡