ግዮን መጽሔት ከጠበቃ መሠረት ሥዩም ጋር የነበራት ቆይታ

Date:

የዛሬዋ የግዮን እንግዳችን መሠረት ሥዩም ትባላለች፡፡ በሙያዋ ጠበቃና የሕግ አማካሪ ናት፡፡ አጭር በሚባሉ ዓመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ ተሻግራ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተጽዕኖ ፈጣሪ ሥራ መሥራት የቻለች ኢትዮጵያዊት ናት፡፡

መሠረት በግል ጥረቷና ትጋቷ የጀመረችውን ሥራ ዛሬ ወደ ተቋም በማሳደግ ‹‹ማኩታ›› የተሰኘ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሕግ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት መገንባት ችላለች፡፡ በቀጣይም በሉላዊ ደረጃ ትልልቅ የሚባሉ የሕግ ጉዳዮችን ለመያዝ የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪ መሠረት ስለሕግ የበላይነት እና ስለ ፍትሕ መረጋገጥ ጽኑና የቆየ መርኅ ያላት ሴት ናት፡፡ ለመኾኑ ከየት ተነስታ ዛሬ ያለችበት ቁመና ደረሰች? የልጅነትና የሥራ ሕይወቷን በተመለከተ ከግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር የሚከተለውን ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡ መልካም ንባብ!


ግዮን፡- እንግዳችን ለመኾን ስለፈቀድሽ እናመሰግናለን፡፡ ራስሽን በማስተዋወቅ ብትጀምሪ?


መሠረት፡- ጠበቃ መሠረት ሥዩም እባላለሁ፡፡ ተወልጄ ያደግኩት ፍቼ ከተማ ነው፡፡ እድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ ትምህርት ቤት ገሁ፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም አጠናቅቄ ስጨርስ የመጀመሪያ ዲግሪ የሕግ ትምህርት ተምሬ ወደ ሥራ ገባሁ፡፡ እየሰራሁ የሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ በኢንተርናሽናል ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አጠናቅቄአለሁ፡፡

ብዙ ጊዜዬን ያሳለፍኩት በሥራ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ ፍቼ ከተማ በንግድ ሥራ የተሰማሩ ናቸው፡፡ እነሱን በሥራ የማገዝ ተግባር ስፈጽም አድጌያለሁ፡፡ አስተዳደጌን በጣም እወደዋለሁ፡፡ በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ውስጥ የማደግ እድል አግኝቻለሁ። በጣም ፍቅር እና ደስታ የተሞላበት ደግሞም ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ያለበት አስተዳደግ ነው። በአደግሁበት አካባቢም እኔ የተማርሁት ሰዎች ሰርተው ሲለወጡ፣ ሲተጋገዙ፣ ደስታንና ሃዘንን አብረው ሲካፈሉ ነው፡፡ በጣም የቅንነት፣ የደግነት ጣራ ያየሁበት የልጅነት እድሜን ነው ያሳለፍሁት።


ግዮን፡- ቤተሰባዊ ሕይወታችሁና የልጅነት ዘመንሽ በምን መልክ አለፉ?


መሠረት፡- እንደማንኛውም ልጅ ከቤተሰቤ ጋር ነው የኖርሁት፡፡ በጣም የምወዳቸው እናት እና አባት፣ አምስት እህቶች እና ሁለት ወንድሞችም አሉኝ፡፡ እርስ በእርሳችን እንደ ወንድም እና እህት ብቻ ሳይሆን እንደ ጓደኛሞችም በጣም እንቀራረባለን፡፡

እናቴ በጣም አስተዋይ፣ ሳቂታ እና ብልህ ሴት ናት፡፡ በጣም የሥራ ሰው ነች፡፡ አባቴ በጣም ደግ እና ዘመናዊ የሚባል ዐይነት አባት ነው። ፍቅር ይሰጠን ነበር። ከግቢ መውጣትን ሳይጨምር ተገቢውን ነጻነት ይሰጠን ነበር። በራስ መተማመን እንዲኖረን አድርጎም ነበር። ብዙ ትዝታዎች አሉኝ።


እያንዳንዱ ዕለት የየራሱ ዐውድ አለው፡፡ ለምሳሌ በየሳምንቱ አርብ በቴሌቪዥን የሚተላለፍ ‹‹ሪሲሊንግ›› የሚባል ፕሮግራም አለ፡፡ ሳሎን ቁጭ ብለን ቡና እየተፈላ ለጋራ ማዕድ ቀርቦ በሳቅ በጨዋታ ታጅበን ዕለቱን እናሳልፍ ነበር፡፡ ያው አርብ የትምህርት መጨረሻ ቀን ስለኾነ በጉጉት ነበር የምንጠብቀው፡፡

ቅዳሜ ደግሞ በየፊናችን ሱቅ እንሄዳለን፡፡ አባቴ ብቻውን የሸቀጣ ሸቀጥ፣ የሕንፃና የጽሕፈት መሣሪያ ሱቆች ነበሩት፡፡ ሱፐር ማርኬትም ነበረን፡፡ የቡና ነጋዴም ነበር፡፡ የሕንፃ መሣሪያውን ሱቅ የምታስተዳድረው እናቴ ነበረች፡፡ ገበያውም በጣም የደራ ነበር፡፡ ከተማው፣ ቆለኛው ከደገኛው የተለያየ ማንነት ያላቸው ሰዎች ሁሉ የሚሳተፉበትና ተቀላቅለው የሚውሉበት ከተማ ነው፡፡ የሚገርም ሕብረት የሚታይበት ከተማ ነው፡፡

በአጠቃላይ እህትና ወንድሞቼ ሁላችንም በሥራ ነው ያደግነው፡፡ ስንሠራም አባታችንን በጣም ስለምንወደው የምናስደስተው ይመሰለን ነበር፡፡ ቤተሰብም ልጆቹን አስተምሮ ወደ ንግድ ማስገባት የተለመደ አሠራር ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ሁላችንም በትምህርታችን ጠንካሮች ነበርን፡፡ እናቴ አባታችንን በጣም እንድንወደው አድርጋ ነው ያሳደገችን።


ግዮን፡- እንዲህ ካለ የነጋዴ ቤተሰብ ወጥተሽ እንዴት ጠበቃ ለመኾን በቃሽ?


መሠረት፡- ልጅ ኾነን አባቴ ወደነጋዴ ማኅበር ስብሰባ ይልከኝ ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ ለንግግር ፈጣን ስለነበርኩ በማናቸውም ጉዳዮች ዙሪያ ሐሳብ እሰነዝር ነበር፡፡ አባቴም ለእንዲህ ዓይነት መድረክ የምኾን ሰው እንድኾን እየቀረፀ አሳድጎኛል፡፡ እኔም ከልጅነቴ አንስቶ ወደተለያዩ ተቋማት ሄጄ ጉዳዮችን ሳስጨርስ ደስ እሰኝ ነበር፡፡

በባሕሪዬ ሰው መርዳትና ማገዝ ያስደስተኛል፡፡ የሕግ ባለሙያ የመኾን ፍላጎቴ የመጣውም ከዚህ ሰዎችን የማገዝ ብርቱ ፍላጎቴ ነው፡፡
እህትና ወንድሞቼም ቢኾኑ ተምረው በተለያየ ሙያ ላይ ነው የተሰማሩት፡፡ ከእህቶቼ ለመጀመር፣ አንዷ እህቴ አርክቴክት ናት፤ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነው የተማረችው፡፡ አሁን ላይ ብዙ አስገራሚ የአርክቴክቸር ሥራዎችን በራሷ የምትሠራ ሰው ናት፡፡

ሌላኛዋ እህቴ ደግሞ በሙያዋ ሜዲካል ዶክተር ናት፡፡ አሜሪካን ሀገር የምትኖረዋ ሌላኛዋ እህቴም እንዲሁ፣ አስቀድሞ አካውንታንት የነበረች ቢኾንም በቅርቡ ወደ ሕክምናው ዘርፍ መጥታለች፡፡ ሌላኛዋ ኮምፒውተር ሳይንስ አጥንታ፣ ወደ ግል ሥራ የሚያስገባትን ትምህርት ቻይና ድረስ ተምራ ተመልሳ በንግድ ባለሙያነት የተሰማራች ሌላ እህትም አለችኝ፡፡ አንድ ወንድሜ ኑሮውን በካናዳ አድርጎ ማናጀር ኾኖ የራሱን ሥራ እየሰራ ትዳር ይዞ ይኖራል።

እንደ እኔ በተመሳሳይ የሕግ ባለሙያነት ላይ የተሰማራች እህትም አለችኝ፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም ተምረውና ለተወሰነ ጊዜ ተቀጥረው ሰርተው የራሳቸውን ተቋም ወደ መፍጠር ነው ያመሩት፡፡ ይኼ ደግሞ በዋናነት በእግዚአብሔር እርዳታ ነው። በመቀጠል ግን በንግድ ሥራ ላይ እና በነጋዴ ማኅበረሰብ ውስጥ የማደጋችን እንዲሁም የነጋዴ ቤተሰብ ልጆች ኾነን ሥራ እየሰራን የማደጋችን ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡


ግዮን፡- አንቺስ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀሽ መጀመሪያ ሥራ የጀመርሽው የት ነበር?


መሠረት፡- ገቢዎች ሠርቻለሁ፤ ከዚያ ውጭ የተለያዩ ኩባንያዎችን ወክዬ ሠርቻለሁ፡፡ ለአጫጭር ጊዜያትም ቢኾን በመንግሥት ተቋማትም ላይ ሠርቻለሁ፡፡ አብዛኛው ሥራዬ ወደ ግሉ ዘርፍ ያደላል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ዓለም አቀፉ ገበያ ውስጥ የገባሁት፡፡


ግዮን፡- በዐቃቤ ሕግነት አገልግለሽ ታውቂያለሽ?


መሠረት፡- ገቢዎች ስሠራ ጠበቃ ሳልኾን ነገረ ፈጅ በመኾን ነው የሠራሁት፤ በውስጡ ቀጥታ ክስ የሚባል ነገርም ነበረው፡፡ ይግባኝና የመሣሠሉትን በመሥራት የተቋሙ የሕግ ባለሙያ ኾኜ ነው ያገለገልኩት፡፡

ማስታወሻ- ውድ አንባቢያን፣ ከጠበቃ መሠረት ሥዩም ጋር ያደረግነው ክፍል አንድ ቆይታችን ነዉ።፡ በክፍል ሁለት ቆይታችን የሙያና የሕይወቷን እንቅስቃሴዎችና ተሞክሮዎች በተመለከተ በሚቀጥሉት ቀናት የምንመለስ ይኾናል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

30 ሺህ ተሳታፊዎችን የሚያስተናግደው ዓለማ አቀፍ የጤና ጉባኤ ሊካሄድ ነው

የዲፕሎማሲ መዲናዋ አዲስ አበባ 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ...

የመማሪያ ማስተማሪያ መጻህፍት እጥረትን ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ ነዉ

የትምህርት ጥራቱን የበለጠ ለማሻሻል የቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ የመማሪያ...

የፊንቴክ ሥራ አስኪያጅ በከባድ የማታለል ወንጀል ተከሰሰ

​በአዲስ አበባ የፊንቴክ ኢንቨስትመንት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዳንኤል ዮሐንስ፣...

ኢራን በሆርሙዝ በኩል ሊያልፉ የነበሩ ሦስት መርከቦችን መመለሷን አሳወቀች

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዛሬ ጠዋት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል...