የትምህርት ጥራቱን የበለጠ ለማሻሻል የቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ የመማሪያ ማስተማሪያ መጻህፍት እጥረት የታየባቸው የትምህርት አይነቶችንና የክፍል ደረጃዎችን በመለየት ለማሳተም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሥርዓተ-ትምህርት ማበልጸጊያ ተ/ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዛፏ አብርሃ ገልጸዋል።
በዚህም እጥረት የታየባቸውን መጻህፍት በቀጣይ ለማሳተም የክልልና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎችን የህትመት ፍላጎት ልየታ እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
እንደ መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ የመማሪያ ማስተማሪያ መጻህፍት እጥረት የታየባቸው ደረጃዎችንና የትምህርት አይነቶችን ለይቶ ድጋፍ ለማድረግ የትምህርት መረጃ አስተዳደር ስርዓትን በመጠቀም (EMIS) እና ከክልልና ከተማ አሰተዳደር ትምህርት ቢሮዎች በተሰበሰበው መረጃ መሰረት በማድረግ የቅድመ አንደኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት የመማሪያ ማስተማሪያ መጻህፍት ህትመት ፍላጎት እየተለየ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቅድመ አንደኛና አንደኛ ደረጃ የመጻህፍት ተማሪ ጥምርታን 1ለ1 ለማድረስ በተመረጡ አምስት የትምህርት አይነቶች የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ ሂሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ አካባቢ ሳይንስ፣ ግብረገብና የስነ-ጥበብ ትምህርቶች መጽህፍትን ለማሳተም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል
ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ከ23.9 ሚሊየን በላይ የአንደኛ ደረጃ መጽሃፍትን አሳትሞ ለክልሎች እያሰራጨ እንደሚገኘኝ ይታወሳል።
