“በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ከእምብርቷ በላይ አልፈን ነው የሰራነው። በጣም ትልቅ እጢ ሲሆን ይጠማዘዛል ተብሎ ባይታሰብም ግን ሁለት ጊዜ ተጠማዞ ነው ያገኘነው” – 19Kg የማህጸን እጢ ያወጣው ዶክተር
ሙሉ የእርግዝና ክትትል ባለማድረጓ፣ ሳይታወቅ ከጽንስ ጋር ተሸክማው የነበረውን 19 ኪሎግራም የማህጸን እጢ ከአንዲት እናት በቀዶ ህክምና ማውጣቱን ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ገልጿል።
ቀዶ ህክምናውን የሰሩት የማህጸንና ጽንስ ስፓሻሊት ሀኪም፣ በዩኒቨርሲቲው በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሚያስተምሩት ዶክተር ጁሃር መሐመድ ምን አሉ ?
” እናታችን የመጣችው ከገጠር አካባቢ ነው። ከአንድ ወር በፊት ልጅ የወለደችው ሰሜን ወሎ ዞን ግዳን ጤና ጣቢያ ነው። ግን ከወለደች በኋላ ሆዷ አልሟሸሸም፣ እርግዝና እንዳለ አይነት ሆኖ ተወጥሮ ነበር የሚታየው።
ነገር ግን አንዲት እናት ከወለደች በኋላ ማህጸን ተኮማትሮ ወደቦታው ይመለሳል፤ በእርግዝና ወቅት የተወጠረ ሆዷም እየቀነሰ ነው መሄድ ያለበት። የዚችኛዋ እናት ግን ከወለደች በኋላም 30 ቀናት እንዳለ ነው የነበረው።
አዋላጅ ነርሷም ሲያየውም ሆዷ አልቀነሰም። እርሷም ህመም ይሰማታል። የቀረ ነገር እንዳለም ተሰማት። ባለሙያውም ጥሩ ባለሙያ ነው ሳላመሰግነው አላልፍም፤ ማህጸኗ ሳይመለስ የቀረ ነው የመሰለው፣ የሚችለውን አድርጎ ካቅሙ በላይ ሲሆን ለወልዲያ አጠቃላይ ሆስፒታል ሪፈር ጻፈ።
መጥታ ሳያት ነፍሰጡር ነበር የምትመስለው፤ ሆዷ እንደተወጠረ ነበር። ከዚያም አልትራሳውንድ ስካን ሰራሁላት። በአልትራሳውንድ ለመለካት የሚያስቸግር፣ ሙሉ ሆዷን ከማህጸን ማስቀመጫው እስከ ሳምባዋ ድረስ የተወጠረ ሆድ ነው የነበራት።
ምክንያቱም ከእርግዝናው ጋር አብሮ ያደገ የማህጸን እጢ ነበረባት። በጣም ትልቅ (19Kg) እጢ ነው። ሲታይ ከማህጸን ዘር ፍሬ ማምረቻ የተነሳ ውሃ የቋጠረ እጢ ነበር የሚመስለው።
እንደዚህ አይነት ኦፕሬሽኖች መሰራት ያለባቸው ስድስት ሳምንት ከሞላ በኋላ፤ የእርግዝና ጊዜው ካለፈ በኋላ፣ ማህጸን ወደቦታው ከተመለሰ በኋላ ቢሆን ይሻላል ተብሎ ነው የሚመከረው። ግን ሴትዮዋ ስመለከታት ከፍተኛ ህመም ነበራት፤ ሆዷ በጣም ተወጥሮ ነበር፤ የምትመገበው አይስማማትም፤ እስከ ሳምባዋ ስለያዛት ለመመገብም ትቸገር ነበር።
ህመም ካስከተለ እጢው የመጠምዘዝ እድል አለው። ግን ደግሞ እጢው የመጠማዘዝ እድል ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰበው መጠኑ ከ5 እስከ 10cm ሲሆን ነው። ከዚያ በላይ ከሆነ ይጠመዘዛል ተብሎ አይጠበቅም።
ህመሙ ስላለ ስድስት ሳምንት መጠበቅ አልተቻለም። በወለደች በወሯ ኦፕሬሽን ተሰራላት ” ብለዋል።
በቀዶ ህክምና ወቅት ስላጋጠማቸው ነገር ዶክተር ጁሃር ምን አሉ ?
” እጢው በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ከእምብርቷ በላይ አልፈን ነው የሰራነው። በጣም ትልቅ እጢ ሲሆን ይጠማዘዛል ተብሎ ባይታሰብም ውስጥ ስንገባ ግን ሁለት ጊዜ ተጠማዞ ነው ያገኘነው። ግን በጣም ጥብቅ ያለ መጠማዘዝ አይደለም። ህመሙን ያስከተለባት መጠማዘዙ ነበር።
ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ሴትዮዋ እድለኛ የሆነችው ነገር፦ እጢው ሳይፈነዳ ነጥለን ነው በኦፕሬሽን ያወጣንላት። ከወር በፊት ሦስተኛ ልጇን ነው የወለደችው፤ ገና በመውለድ እድሜ ክልል ውስጥ ነች፣ 28 ዓመቷ ነው።
በመውለድ እድሜ ያለን ሰው ማህጸኑ ይተዋል፤ ከ50 ዓመት በላይ ሲሆን ግን እንደዚህ አይነት ነገር ሲያጋጥም ወደ ካንሰር የመቀየር እድል ስለሚኖረው ማህጸን፣ የዘር ፍሬዎች፣ ቱቦዎችም አብረው ይወጣሉ። የሷን ግን እጢ ያለበትን ጎን የማህጸን ቱቦ ማስተላለፊያውን ጨምረን አወጣላት። ምንም ነገር ሳይፈስና ሳይሰራጭ ነው ያወጣንላት።
አብዛኛው ሰው እጢው ከወጣ በኋላ በፌስታል የተቋጠረ ነው የመሰለው። ግን የራሱ የእጢው ከረጢት ነው። በራሱ ከረጢት ነው ቋጥረን ያወጣነው። በጣም ትልቅ ስለሆነ ባንዴ አይወጣም፣ ቀስ እያልን እየገፋን አወጣነው። ስንመዝነው ማመን አልቻልንም፤ ሳፋውን ሞልቶ አልፏል። 19 ኪሎ ግራም ነው። እንደዚህ አይነት ገጠመኝ አጋጥሞን አያውቅም።
አሁን ታካሚዋ በሙሉ ጤንነት ላይ ነች። ልጇንም እያጠባች ነው። ታህሳስ 1/2018 ነው ቀዶ ጥገና የተሰራላት። ወደቤቷ ሄዳለች። በሁሉ ነገር ሰላም ነች” ብለዋል።
የተሰማቸውን ደስታ ስንጠይቃቸውም፦
” ሀኪም ሲኮን ብዙ ነገሮች ያጋጥማሉ፤ የአሁኑ ግን ከሁሉም እርካታው የተለዬ ነው። ስቃዩዋም ብዙ ነበር። ደስታዋን፣ ልጀዋን ስታጠባ፣ በጤና ስትንቀሳቀስ ከማየት የበለጠ ደስታ የለም። የሰው የሰውን ህመም ወደራሱ አምጥቶ አስተያየት የሚሰጠው አስተያየት ሲሰጥ ሲታይ ያስደስታል።
ለካ ከዚህም በላይ በመስራት፣ በተለይ የገጠሩን ማህበረሰብ መድረስ አለብን ያስብላል። የሰው ማበረታታት ጥሩ እንድንሆን ነው የሚያደርገው፤ ለወደፊት ከዚህ በላይ ለመስራት፣ ማህበረሰቡን ለማገልገል ነው የምዘጋጀው ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
