በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተፈናቃዮች የተመደበው ሰብአዊ እርዳታ እንዳልቀረበላቸው ፌደራል ዋና ኦዲተር ገለጸ፡፡
ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ይህንን የገለጸው ትላንት ሰኔ 17 ቀን 2017ዓ/ም ቀን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንን የ2016ዓ/ም የሰብአዊ እርዳታ ስርጭት እና አፈጻጸም ሪፖርትን ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡
ሪፖርቱን ያቀረቡት ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ በ2016 ዓ/ም በሀገሪቱ 2738 የመጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉ እና በነዚህ መጠለያዎች በተደረገ የተረጂዎች ልየታ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን እርዳታ ፈላጊዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
489 ሺህ 290 ከ5 አመት በታች ህጻናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፤ በቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ዋና ኦዲተሯ በሪፖርቱ ላይ አብራርተዋል፡፡
በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች በተደረገ ምልከታም ለአጥቢ እና ነፍሰጡር እናቶች እንዲሁም ከ 5 አመት በታች ህጻናት መሰጠት የሚገባው አልሚ ምግብ ለሁሉም ተፈናቃዮች መሰጠቱ ተገልጿል፡፡ ይህም የተደራሽነት ጥያቄ አስነስቷል።
በዚህም መስሪያ ቤቱ ለናሙና ምልከታ ባደረገበት 10 መጠለያ ጣቢያዎች ህጻናት እና እናቶች የአልሚ ምግብ ካገኙ ሁለት አመት እንደሆናቸው ተገልጿል፡፡
