በዝግጅቱ ላይ የስኳር ህመምን ለመከላከል ቅድመ ምርመራን፣ ጤናማ አመጋገብንና መደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴን ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።
በከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶች፣ የእግረኛ መንገዶች እና የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች መስፋፋት ሰዎች በየዕለቱ እንዲንቀሳቀሱና አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በሽታውን ለመከላከል ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።
የጤና ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፥መደበኛ የእግር ጉዞና አካላዊ እንቅስቃሴ ሰውነት ኢንሱሊንን በተሻለ ሁኔታ እንዲጠቀም በማድረግ በደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር ያግዛል።
በመሆኑም የከተማ ልማት ሥራዎች ከመልክና ከመሠረተ ልማት ጥቅማቸው ባሻገር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል ረገድም ጠቃሚ መሆናቸው በመድረኩ ላይ ተነስቷል::
በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአዕምሮ ጤና ዴስክ ቡድን መሪ ዶክተር ሰላማዊት አየለ፥ህመሙ በኢትዮጵያ እየጨመረ መምጣቱንና በተለይም በሀገሪቱ የምርታማ ኃይል ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን የገለፁ ሲሆን፥መንግሥት በሽታውን በፖሊሲና በስትራቴጂ ለመከላከል እንዲሁም የሕክምናና የመድኃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያደርገውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ በበኩላቸው፥የስኳር ህመም ቀን በሽታውን በቅድሚያ ለመከላከልና ስለህመሙ ግንዛቤን ለማስፋት ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
ማህበሩም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ነፃ የስኳር ህመም ምርመራ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመድረኩ ሕብረተሰቡ የህመሙ ምልክት እስኪታይ ድረስ ሳይጠብቅ በቅድሚያ የጤና ምርመራ እንዲያደርግ፣ አመጋገቡን እንዲያስተካክል እና መደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴን እንዲያዘወትር ጥሪ ቀርቧል።
