የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) በሥሩ ለሚገኙ 41 የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የደመወዝ ጭማሪ፣ ዓመታዊ ቦነስና ሌሎች ማበረታቻዎች በውጭ ኦዲተሮች በተረጋገጠ የሒሳብ ሪፖርትና በተጣራ ትርፍ ላይ ተመስርተው ብቻ እንዲፈጸሙ መመሪያ አውጥቷል።
ኅዳር 8 ቀን 2019 ዓ.ም. በዋና ሥራ አስፈጻሚው ብሩክ ታዬ የተፈረመው መመሪያ፣ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ ተቋማት ጊዜያዊ የሒሳብ ሪፖርቶችን ወይም ጠቅላላ ገቢን ብቻ መሠረት በማድረግ ክፍያ እንዳይፈጽሙ ይከለክላል። ክፍያዎቹ ከመፈጸማቸው በፊት የተጣራ ትርፍ መመዝገብ፣ የንግድ ዕቅድ መሳካትና በቂ የጥሬ ገንዘብ አቅም መኖር እንዳለበት ተቀምጧል።
መመሪያው በሠራተኛ ማኅበራት ዘንድ ስጋት የፈጠረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ድሪብሳ ለገሠ እንደገለጹት፣ የውጭ ኦዲት ሒደት ከሁለት እስከ አራት ዓመት የሚዘገይባቸው ተቋማት በመኖራቸው፣ ሠራተኞች የሥራ ኢላማቸውን ቢያሳኩም ጥቅማጥቅማቸውን በወቅቱ ላያገኙ ይችላሉ።
ሆልዲንግሱ በበኩሉ የድርጅቶቹ ቦርዶችና ከፍተኛ አመራሮች መመሪያውን በተቋማዊ ፖሊሲዎች፣ በአሠራር መመሪያዎችና በኅብረት ስምምነቶች ውስጥ እንዲያካትቱ አሳስቧል።
