የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ12ኛው ዙር 92 የሕክምና ዶክተሮችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ 36ቱ ሴቶች ናቸው።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ሁለት ሴት ሐኪሞች የዕለቱ ልዩ ተሸላሚዎች ሲሆኑ፣ የአንደኛነትና የሶስተኛነት ደረጃዎችንም ሴት ተመራቂዎች ተቀዳጅተዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ዶክተር እጹብ ስንታየሁ 3.86 ከ4.00 ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በሜዳሊያ ተመርቃለች። የትምህርት ጉዞዋን በዚህ ውጤት ማጠናቀቋ የጥረቷ ፍሬ በመሆኑ ታላቅ ደስታ እንደተሰማት ገልጻለች።
ዶክተር እጹብ የትምህርት ጉዞዋ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በተለያዩ ፈተናዎች የታጀበ ቢሆንም፣ በወቅቱ ብዙ ዕውቀትና ልምድ ማግኘቷን ተናግራለች።
“3.86 በሕይወቴ ትልቅ ትርጉም ፈጥሮ ሕይወት ለማዳን አዘጋጅቶኛል” ያለችው ዶክተር እጹብ፣ የሕክምና ሙያ ሰዎችን በማከም፣ ሕይወትን በማዳንና በማገልገል ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጻ፣ በቀጣይም ሕዝብን በማገልገልና የሀገርን አደራ በመወጣት ለሙያው ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጣለች።
