የሕንድ ጨርቃጨርቅ ግዙፍ ኩባንያ የሆነው ሬይመንድ ሊሚትድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሕንድ ምርቶች ላይ በጣለችው አዲስ ታሪፍ ምክንያት፣ የምርት ሂደቱን በከፊል ወደ ኢትዮጵያ ለማዛወር እያሰበ መሆኑን ገለጸ።
ይህ እርምጃ ኩባንያው የአሜሪካንን የንግድ ፖሊሲ ለውጥ ለመቋቋም እንደ ስልታዊ አማራጭ አድርጎ የተመለከተው ነው።
የኩባንያው የፋይናንስ ኦፊሰር የሆኑት አሚት አጋርዋል እንደተናገሩት፣ ኩባንያው አሁን ያለውን ሁኔታ በረጅም ጊዜ እቅድ መሠረት እየተመለከተው ነው።
የኩባንያው አጠቃላይ የልብስ ገቢ ከ50-55% የሚሆነው ከአሜሪካ እንደሆነ ገልጸው፣ ከዚህ ውስጥ 30% የሚሆነው ምርት ቀደም ሲልም ከኢትዮጵያ በሚገኘው ፋብሪካቸው ሲመረት እንደነበር አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ፋብሪካ ከህንድ ምርት ወደ እሱ እንዲዘዋወር የሚያስችል ተጨማሪ አቅም እንዳለውም ጠቅሰዋል። ይህም ኩባንያው በአሜሪካ ታሪፍ ምክንያት የሚመጣውን ተግዳሮት ለመቋቋም ትልቅ ተለዋዋጭነት እንደሚሰጠው ተጠቁሟል ። ኩባንያው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ባንግላዴሽ እና ቬትናምን እንደ አማራጭ እያየ እንደሆነም ተገልጿል።
