በኬንያ አስተናጋጅነት ከነሐሴ 29/2017 እስከ መስከረም 04/2018 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ክለቦች (ሴካፋ) ሻምፕዮና ውድድር ላይ ተካፋይ ለሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በራዲሰን ብሉ ሆቴል የሽኝት ስነ ስርዓት ተደርጎለታል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ም/ፕሬዚዳንት እና የባንኩ ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሚደቅሳ ቶሎሳ ቡድኑ በድል እንደሚመለስ ያላቸውን እምነት ገልፀው፣ የባንኩ ድጋፍ እንደማይለያቸው አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቢዝነስ ኤክስኪውቲቭ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ደረጄ ፉፋ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የባንካችንም የሃገራችንም ኩራትና ምሳሌ ናቸው ብለዋል፡፡
አቶ ደረጄ ቡድኑ የተሰጠውን ኃላፊነት በትጋትና በብስለት እንዲሁም በጥሩ ስነ ምግባር በመወጣት በድል እንደሚመለስ ተስፋቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“በሀገራችን እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ውጤታማ የሆነ የለም” በማለት ቡድን ያወደሱት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሳያ ጂራ፤ ቡድኑ ያለፈውን ዓመት ልምድ ተጠቅሞ ሻምዮናነቱን ዘንድሮም በማስጠበቅ ታሪክ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የቡድኑ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውና ተጫዋቾች በበኩላቸው ባንኩ በሁሉም ረገድ ድጋፍ እንዳደረገላቸውና የአምናውን ድል በመድገም በድጋሚ የባንኩንና የሀገራቸውን ስም ከፍ ለማድረግ እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አምና በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የሴቶች እግር ኳስ ክለቦች ሻምፕዮና የነበረ ሲሆን፣ የዘንድሮ አሸናፊም በካፍ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ውድድር ላይ ምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካን በመወከል ተሳታፊ ይሆናል፡፡
