በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት፣ ሩሲያ በዩክሬን መሠረተ ልማቶች ላይ በምትሰነዝረው ድንገተኛ የድሮን ጥቃት ምክንያት፣ የሮማኒያ አየር ክልል ጥሰት እንደተፈጠረ የሮማኒያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህን ተከትሎም የኔቶ አባል የሆነችው ሮማኒያ ሁኔታውን ለመከታተል ተዋጊ ጄቶቿን ወደ አየር አውጥታለች።
የመከላከያ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፣ ሁለት F-16 ተዋጊ ጄቶች ወደ አየር ከተላኩ በኋላ፣ በሮማኒያ አየር ክልል ውስጥ የነበረ አንድ ድሮን መለየታቸውን እና ከራዳር እስኪጠፋ ድረስ መከታተላቸውን ገልጿል።
ድሮኑ ከቺሊያ ቬቼ መንደር አቅራቢያ ከራዳር ውጪ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቆመው።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ የሩሲያ ድሮን ከሮማኒያ ግዛት እስከ 10 ኪሎ ሜትር ዘልቆ መግባቱን እና ለ50 ደቂቃ ያህል በኔቶ አየር ክልል ውስጥ እንደቆየ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቅሰዋል።
ፕሬዝደንቱ ይህንን ድርጊት ሩሲያ ጦርነቱን እያሰፋች እንደሆነ የሚያሳይ ነው ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል።
ይህ ክስተት ፖላንድ የሩሲያን ድሮኖች አየር ክልሏን ከጣሱ በኋላ የኔቶን ምስራቃዊ ድንበር ለመከላከል ዕቅድ መያዙን ካስታወቀች ከጥቂት ቀናት በኋላ መከሰቱ፣ በአካባቢው ያለውን ውጥረት የበለጠ አባብሶታል ሲል መናኸሪያ ሬዲዮ ዘግቧል።
